ፈረንሳይ ለጃዝ ሙዚቃ ንጉስ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እውቅና ሰጠች - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሳይ ለጃዝ ሙዚቃ ንጉስ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እውቅና ሰጠች

መስከረም 8/2012 የፈረንሳይ መንግሥት ታዋቂው የጃዝ ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ በዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽዖ እውቅና ሰጠ። ሙላቱ አስታጥቄ በ1950 ዎቹ የሙዚቃ ትምህርቱን በአሜሪካና በእንግሊዝ አገር በሚገኙ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ተምሯል። ከትምህርት ጎን ለጎንም በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር ሥመ-ጥር ከሆኑ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር በመሥራት ልምዱን አካብቷል። ይህንንም ተከትሎ በሙዚቃ ደራሲነት፣ አቀናባሪነት፣ በቶም ቶም ጨዋታ፣ በፒያኖ ብቁ መሆኑ ተመስክሮለታል። የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ ሥልት በተለይም ከላቲን አሜሪካ ሙዚቃ ጋር በማዋሃድ ኢትዮ-ጃዝ የሚባል ጣምራ የሙዚቃ ሥልት ፈጥሯል። በዚህም "አፍሮ ላቲን ሶል" ቁጥር 1 እና 2 እንዲሁም "የካቲት ኢትዮ-ጃዝ" የሚባሉት የሙዚቃ ሥራዎቹ ተወዳጅ ናቸው። በተለያዩ አገሮች በመጓዝ የሙዚቃ ሥራዎች በማቅረብ ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀው አርቲስት ሙላቱ፤ በርካታ ሽልማቶች አግኝቷል። አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ዛሬ ደግሞ የፈረንሳይ መንግሥት ለሥራው እውቅና ሰጥቶታል። አዲስ አበባ በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ዛሬ በተካሄደው መርኃ ግብር አርቲስ ሙላቱ አስታጥቄ የእውቅና ሽልማቱን ተቀብሏል። የፈረንሳይ የባህል ሚኒስትር ፍራንክ ሪስተር፤ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ አንጋፋና እውቅናን በዓለም ያተረፈ መሆኑን መስክረዋል። ''የፈረንሳይ መንግሥት አርቲስት ሙላቱ ለዓለም ሙዚቃ ላበረከተው አስተዋጽኦ የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት ሰጥቶታል ነው'' ብለዋል። አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄም በተበረከተለት ሽልማት የተሰማውን ደስታ እንዲሁም ለፈረንሳይ መንግሥትና ሕዝብ አክብሮቱን ገልጿል። አርቲስቱ ሙላቱ በቅርቡ በስፔን የጃዝ ሙዚቃ ሥራውን ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ በቬትናም እንዲያቀርብ ጥያቄ እንደቀረበለት ተናግሯል። በመርኃ ግብሩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯን ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች ተገኝተዋል።