ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ
መስከረም 8/2012 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ኡሚ አባጀማል እንዳሉት ከብራዚል ሳዖፖሎ አዲስ አበባ የገባው 8 ኪሎ ግራም የኮኬይን አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ የጉምሩክ ፈታሾች በቁጥጥር ስር ውሏል። ዕፁን ይዞ ይጓዝ የነበረዉ ግለሰብ ላይ ከብራዚል ሳኦፖሎ ጀምሮ የጉምሩክ ኮሚሽን ኢንተለጀንስ ቡድን ባደረገዉ የተቀናጀና ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን ጠቁመዋል። ይህንን አድካሚና የተቀናጀ ስራ በመስራት እፁን መያዝ ለቻሉ የቦሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራርና ሰራተኞች ሚኒስቴሩ አመስግኗል። ባለፈዉ ሳምንትም 20 ሚሊየን ብር የሚገመት 10.8 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ መያዙ የሚታወስ ነው፡፡ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ህግን ለማስከበር እየሰራ ባለው ስራ ቀደም ሲል በርካታ በአገር ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑም ታውቋል።