ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የቤተመንግስት እድሳት ዙሪያ ከፈረንሳይ የባህል ሚንስትር ጋር ተወያዩ

114
መስከረም 8/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ በመከናወነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የኢዩቤልዩ ቤተመንግስት እድሳት ዙሪያ ከፈረንሳይ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር ጋር ተወያዩ። የቱሪዝም ዘርፍን ማጎልበት ለሥራ ፈጠራና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መንግስት እያደረጋቸው ካሉ እንቅስቃሴዎች ዋነኛው ነው:: ለዚህም የቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ቅድሚያ የሚሰጠው የዘርፉ አካል መሆኑ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት ከፈረንሳይ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተገናኝተው በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የኢዩቤልዩ ቤተመንግስት እድሳት ዙሪያ መክረዋል። በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እድሳቱን ማፋጠን እንዲቻል ያበረታቷቸው መሆኑን ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የኢዩቤልዩ ቤተመንግስት እድሳት በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ  የሚከናወን ነው። የኢትዮጵያና የፈረንሳይን ጠንካራ ግንኙነትና የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጥልቅ የትብብር ፍቃደኝነት እድሳቱ እውን እንዲሆን አስችሎታል። የፈረንሳይ የባህል ሚንስትር ፍራንክ ራይስተር በበኩላቸው የጉብኝታቸው ምክንያት ፕሬዝዳንት ማክሮን ለሁለቱም ሀገራት የሚበጅ የቅርስ ጥበቃ ላይ ለመተባበር ያላቸውን ፍቃደኝነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የቅርስ ጥበቃ ላይ የሁለቱ አገሮች ትብብር የቴክኒክና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል። የኢዩቤልዩ ቤተመንግስት እድሳትን በተመለከተ አስፈላጊው ጥናት እየተጠናቀቀ ሲሆን እድሳቱ በጥቂት ወራት ውስጥ ተጀምሮ ተጠናቆ ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል። እድሳቱ የሚከናወነው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢተዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በገቡት ቃል መሰረት መሆኑ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም