በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት መቸገራቸውን የሰቀላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት መቸገራቸውን የሰቀላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
መስከረም 8/2012 በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት ምክንያት ለተለያየ ችግር መዳረጋቸውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አንዳንድ የሰቀላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡ የነዋሪዎችን ችግር ለማቃለል በከተማው በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ገልፀዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ጡረ ፍቃዱ እንደገለፁት በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ንጽህናው ያልተጠበቀ አንድ ጀርካን ውሃ በ10 ብር ገዝተው እየተጠቀሙ ነው፡፡ በተጨማሪም ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ከቤት ክዳን ቆርቆሮ የሚወርደውን የዝናብ ውሃ እያጠራቀሙ እንደሚጠቀሙ ገልጸው ከወዲሁ መፍትሄ ካልተሰጠው መጪው በጋ በመሆኑ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ ኡስማን አህመድ በበኩላቸው በከተማው ከፍተኛ የሆነ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር በመኖሩ ንጽህናው ያልጠተበቀ የወራጅ ወንዝ ውሃ ለመጠጥነት በማዋል ቤተሰባቸው ለውሃ ወለድ በሽታ መጋለጡን ተናግረዋል፡፡ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የሚጠቀሙበት ወራጅ ወንዙ በጎርፍ እንደሚሞላና ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱንም አስታውቀዋል፡፡ የሁለት ሰዓት መንገድ ተጉዘው ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ ቀድተው እንደሚጠቀሙ የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ላኢላ ሁሴን ናቸው ፡፡ የከተማው ከንቲባ ወይዘሮ አየለች በቀለ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩ የተከሰተው ከሁለት ዓመት በፊት በዋን ዋሽ ፕሮግራም በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በመጓተቱ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲጠናቀቅ በማድረግ የሕዝቡን ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ የውሃ ሀብት ልማና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ አብደና ያዴሣ በበኩላቸው ግንባታው ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ኘሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ጊዜ ከ60 በመቶ በላይ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ሥራው በሙሉ መጠናቀቁን የገለጹት ቡድን መሪው ግንባታው በዚህ ኣመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል ፡፡