ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ ለ6 ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

መስከረም 8/2012 በደሴ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ 6ሺህ 500 የችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃለፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዉ የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ወላጆች ልጆች በመለየት ድጋፍ ለማድረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በተደራጀ መንገድ በተደረገው እንቅስቃሴም ባለሃብቶችን፣ ድርጅቶችን፣ ፋብሪካዎችን፣ ነጋዴዎችና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በማስተባበር ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ መሰብሰብ ተችሏል። የተገኘውን ድጋፍም በየቀበሌው የተለዩ  ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ሙሉ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። የተደረገው ድጋፍም የተማሪዎችን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ መረዳዳትን፣ ወገንተኝነትን፣ አንድነትንና ትብብር ለተማሪዎች ለማስተማርም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸዉ ''ተማሪዎች ለትምህርታቸው ብቻ እንጅ ለቁሳቁስ ማሰብ የለባቸውም'' ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተወዳዳሪና ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት በማህበረሰብ አገልግሎት በኩልም የድርሻዉን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ዩኒቨርስቲው ከ350 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጭ አንድ ሺህ 200 የችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸዉን ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸዉ ተማሪዎች ወላጆች መካከል ወይዘሮ ፀሐይ ተፈራ በበኩላቸው ለልጆቻቸዉ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ስለሚቸገሩ በወቅቱ ትምህርት ቤት አንደማይልኳቸዉ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ የተደረገላቸዉ ድጋፍም 400 ብር በላይ ወጭ ያስወጣቸው እንደነበረ ገልጸው ለድጋፉ አመስግነዋል፡፡ ተማሪ ቃል ኪዳን ዳዊት የ5ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የተደረገላት ድጋፍ እንደሌሎች ጓደኞቿ በወቅቱ ትምህርት ቤት ገብታ ለመማር እንደሚያስችላት ገልፃለች። ከተማ አስተዳዳሩ በቀጣይ ጥር ወርም ሁለተኛ ዙር ድጋፍ ለማድረግ እቅድ እንዳለው ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም