ቀጥታ፡

'ተስፋ አይ ኤል ጂ' ድርጅት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል የመገንባት እቅድ እንዳለው ገለጸ

መስከረም 7/2012 መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው 'ተስፋ አይ ኤል ጂ' የተሰኘ ድርጅት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል የመገንባት እቅድ እንዳለው አስታወቀ። ድርጅቱ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጀማሪዎችን በተለያየ መልክ ለመደገፍ የሚያችለውን ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ዛሬ ተፈራርሟል። ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር እና የ'ተስፋ አይ ኤል ጂ' ፕሬዝዳንት ዳዊት ተስፋዬ መፈራረማቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ በስዊዘርላንድ ለቴክኖሎጂ ጀማሪዎች የቴክኖሎጂ ሃሳቦቻቸውን ከመነሻ ጀምሮ ወደ ገበያ እስኪገቡ ድረስ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ነው። በኢትዮጵያም የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን እንዲያዳብሩ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ስልጠና መስጠት፣ ለፈጠራ ባለሙያዎች ስራዎቻቸው ወደ ምርት እንዲገቡ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ፤ የንግድ እቅድ አሰራር ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ ማድረግ የስምምነቱ አካል ነው። 'ተስፋ አይ ኤል ጂ' በስዊዘርላንድ ደረጃ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል በኢትዮጵያ የመገንባት እቅድ እንዳለውም ይፋ አድርጓል። ሚኒስትር ዴኤታው ጀማል በከር ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ፈጠራን እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 'ተስፋ አይ ኤል ጂ' የስዊዘርላንድ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በጋራ እንዲሰሩ የማድረግ እቅድ እንዳለውም ማስታወቁን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም