ቀጥታ፡

ባለፉት ሁለት ወራት ከቡና ንግድ 183 ነጥብ 57 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ   መስከረም 7/2012   ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ሁለት ወራት 52 ሺህ 300 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 183 ነጥብ 57 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡ አፈፃፀሙ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተላከው ጋር ሲነፃፀር በመጠን በ6 ሺህ 585 ነጥብ 14 ቶን ጭማሪ፤ በገቢ ደግሞ በ6 ነጥብ 05 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ ባለስልጣኑ ከእቅዱ በላይ 108 ነጥብ 59 በመቶ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከታቀደው ገቢ 91 ነጥብ 33 በመቶ የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ተችሏልም ብሏል፡፡ ወደ ውጪ ከተላከባቸው አገራት መካከልም ጀርመን ገቢ ማስገኘት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ባለሥልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ የቡና ወጪ ንግድ መዳረሻ ሃገራት ጀርመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጃፓን፣ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ የተቀሩት አሜሪካ፣ ቤልጅየም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ሱዳን፣ ፈረንሳይና አውስትራሊያ በቅደም ተከተል እስከ 10 ያሉትን ደረጃ መያዛቸውን ባለሥልጣኑ አመልክቷል፡፡ በእነዚህ መዳረሻ አገራት ረገድም ከ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በመጠን 34 በመቶ እና በገቢ 14 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም