'አባይ ኢንዱትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር' የተሰኘው ኩባንያ ሦስት የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ምርት ፍቃድ ተሰጠው - ኢዜአ አማርኛ
'አባይ ኢንዱትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር' የተሰኘው ኩባንያ ሦስት የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ምርት ፍቃድ ተሰጠው
መስከረም 7/2012 የመንግሥት ልማት ድርጅቶችና የግል ባለኃብቶች ጥምረት የሆነው 'አባይ ኢንዱትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር' ሦስት የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ምርት ፍቃድ አገኘ። ማህበሩ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ መዋእለ ንዋይ የማምረት ተግባሩን ያከናውናል ተብሏል። የአክሲዮን ማህበሩ በማዕድን ምርት ለመሰማራት የሚያስችለውን ስምምነት ዛሬ ከፌዴራል የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱን የፈረሙት የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ተሻገር እና የማእድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ናቸው። በስምምነቱ መሰረት ማህበሩ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የከፍተኛ ደረጃ ሸክላ አፈር፣ የከፍተኛ ደረጃ የኖራ ድንጋይና ከፍተኛ ደረጃ ጂፕሰም ያመርታል። ማህበሩ የማእድን ምርቱን በአማራ ክልል እያስገነባው ላለው የሲሚንቶ ፋብሪካ ግብኣት ከመጠቀም ባሻገር ለውጭ ገበያው የማቅረብ እቅድም አለው ተብሏል። አክሲዮን ማህበሩ አጠቃላይ ሥራውን የሚያከናውነው ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ መዋእለ ንዋይ ሲሆን ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በስምምነቱ ላይ ተገልጿል። የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ደምስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ማህበሩ በአማራ ክልል የሲሚንቶ እጥረትን ያቃልላል የተባለ ፋብሪካ እያስገነባ ነው። በቀን 2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ይኖረዋል የተባለው ፋብሪካው በሁለት ዓመት ከግማሽ በሆነ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል። የዛሬው ስምምነትም ለፋብሪካው የምርት ግብዓት አስፈላጊ የሆነውን ጥሬ እቃ በሰፊው ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አቶ ደምስ ገልጸዋል። በሚኒስቴሩ የማዕድን ፍቃድ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ልዑል ገብሬ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሥራ ለመጀመር፤ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ወደምርት ለመግባት ውሉ ያስገድዳል። በኢትዮጵያ ዘጠኝ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቢኖሩም በግብዓት እጥረት ምክንያት በሚጠበቀው መጠን እየሰሩ አይደለም ሲሉ አቶ ልዑል ተናግረዋል። ይህም አገሪቷ ለሲሚንቶ ምርት ወደውጭ በማማተር ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ውጪ እየተዳረጋት መሆኑን አመልክተዋል። ማህበሩ በዘርፉ የጀመረው እንቅስቃሴ የምርት አቅርቦትን በማሻሻል በውጭ ምንዛሬ በኩል አገሪቱ ያለባትን ጫና ለማቃለል አወንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል። አክሲዮን ማህበሩ በውሉ መሰረት የአከባቢ ጥበቃን ጨምሮ ሌሎች ግዴታዎችን በማክበር መስራት እንዳለበት ያስገነዘቡት ደግሞ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ናቸው። መንግሥት በነዳጅና ማዕድን ዘርፍ የአገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶችን በስፋት ለማሳተፍ የተለያዩ የአሰራርና ሕግ ማሻሻያ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ከዘርፉ አሰራር ጋር በተያያዘ የነበሩ ክፍተቶችንና ማነቆዎችን በመለየት የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት። በዘርፉ መሰማራት የሚሹ ባለኃብቶች ከሚኒስቴሩ ጋር በቀላሉ የሚገናኙበት አመቺ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱንም አንስተዋል። ሚኒስቴሩ በመስኩ ለሚሰማሩ ኩባንያዎችን ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል አረጋግጠዋል።