ቀጥታ፡

ሐይቅ ከተማ የተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

መስከረም 7/2012 በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ። የሐይቅ ከተማ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ስልጣኑ አባተ እንደገለጹት በመሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት የከተማው ህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በተደረገ ጥረት የ716 ሜትር ርዝመት ያለው የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ተከናውኖ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም 750 ሜትር የጎርፍ መፋሰሻ ካናል፣ ሦስት የመሸጋገሪያ ድልድዮች ግንባታ፣ የጠጠር መንገድ ጠረጋና የማስተካከል ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተከናውነው ለአገልግሎት መብቃታቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማቃለል እንዳስቻለ አስታውቀዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸዉ በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በታቀደላቸዉ ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ የህብረተሰቡ ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ልማቶችም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ከለላና ጥበቃ በማድረግ ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ሰላም ካለ ማንኛውም የልማት ጥያቄ በሂደት ይፈታል ያሉት አቶ ሰጥድ ህብረተሰቡ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡ በሐይቅ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አሊ ይማም በሰጡት አስተያየት በአካባቢያችው የተሰራው የጎርፍ መፋሰሻ ካናል ለረዢም ጊዜ ጥያቄያቸው ምላሽ በመስጠት ከዚህ በፊት የነበረባቸውን የጎርፍ አደጋ ስጋት እንዳስቀረላቸው ገልፀዋል፡፡ ካናሉ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥም ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ ሌላዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ረሂማ ያሲን በበኩላቸው በቀበሌያቸው የተሰራው ዘመናዊ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ከጭቃና ከአቧራ እንደታደጋቸው ገልጸዋል፡፡ መንገዱ ሲሰራም ቁሳቁስ በማቅረብና ደንብ በማስከበር የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በሐይቅ ከተማ በ2012 የበጀት ዓመት በ22 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማካሄድ መታቀዱን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ  ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም