ቀጥታ፡

ለዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከ300 በላይ ድርጅቶች የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎቻቸውን አቀረቡ

መስከረም 7/2012  ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከ300 በላይ ድርጅቶች የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎቻቸውን በመላክ የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ አቀረቡ። ፕሮጀክቶቹን ያቀረቡት ህጋዊ እውቅና ያላችው መንግስታዊ ያልሆኑ እና ሀገር በቀል የልማት ድርጅቶች ናቸው። የህዝብና የሞያ ማህበራት፣ የፌደራል፣ የክልል እና የአካባቢያዊ የመንግስት ተቋሞች እንዲሁም ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን የሚተገብሩ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ናቸው። ድርጅቶቹ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጋር አብረው ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ለትረስት ፈንዱ የቀረቡት የፕሮጀክት  ፕሮፖዛሎች ቁጥር ከተጠበቀው በላይ ከፍተኛ መሆኑንም አመልክቷል። በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን አንገብጋቢ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል  ትረስት ፈንዱ የሚያደርገውን ጥረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የተጠናከረ ድጋፍ የሚጠይቅ ይሆናል። በተጨማሪም በርካታ ተቋሞች ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጋር አብሮ በመስራት የተጀመረውን ወገንን የመታደግ እንቅስቃሴ ለማገዝ ያላቸውን ፍላጎት፤በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያመለክትም ጠቅሷል። ትረስት ፈንዱ በ77 ሀገራት ውስጥ ከሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ካሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል። የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለሚፈቱ ፕሮጀክቶች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ በትጋት እየሰራ ይገኛልም ተብሏል። የፕሮፖዛል ምዘና እና የመረጣ ስራው ፍትሃዊ እና ግልፅነትን በተላበሰ መንገድ የሚከናወን መሆኑም ታውቋል። በዚህ ሂደት በፕሮጀክት ቀረጻ፣ ትግብራና ግምገማ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ባለሞያዎችን በበጎ ፈቃደኘነት ግዜያቸውን እና ለረጅም ዓመት ያካበቱትትን ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተጠይቋል። የፕሮጄክቶች ምዘና እና መረጣ ቡድኑም የፊታችን አርብ ከጽህፈት ቤቱ አመራሮች ጋር ስለ አጠቃላይ ሂደቱ ውይይት ያደርጋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ባወጣዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በቀጣይ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ  ስራውን አጠናቅቆ  የመረጣቸውን ፕሮጀክቶች ለዳይሬክተሮች ቦርድ ለውሳኔ ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል። በቦርዱ ይሁንታ ያገኙ ፕሮጀክቶች ከነዝርዝር መረጃቸው በህዳር 2012 ዓ.ም ይፋ ይደረጋልም ተብሏል። ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የፍይናንስ ድጋፍ የሚያኙ ፕሮጀክቶችን ትግበራ ለማረጋገጥም የክትትልና ግምግማ ስርዓት ይዘረጋል ብሏል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማት እና እድገት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገላቸውን ሀገራዊ ጥሪ ትከትሎ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በዳያስፖራው አማካሪ ምክር ቤት የተቋቋመ ድርጅት ነው። ከማንኛውም ፖሊቲካዊና ኃይማኖታዊ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ፣ ለትርፍ ያልተደራጀና መንግስታዊ ያልሆነ የልማት ድርጅትም ነው፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም