የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት በእጅጉ ያነሰ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት በእጅጉ ያነሰ ነው ተባለ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2012 የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት በእጅጉ ያነሰ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ያካሄደው ጥናት አመለከተ። የጤና ሚኒስቴር የ2009 ዓ.ም የአገሪቱ ዜጎችን የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪን በማስመልከት ለሰባተኛ ጊዜ ያካሄደውን ጥናት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት የታዳጊ አገሮች የነፍስወከፍ የጤና ወጪ ከ86 ዶላር ማነስ የለበትም። ሆኖም ዛሬ ይፋ የሆነው ጥናት እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ 33 ነጥብ 21 ዶላር ብቻ ነው። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ጥናቱ ይፋ በሆነበት ስነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት አዲሱ ጥናት በ2006 ዓ.ም ከተካሄደው ተመሳሳይ ጥናት ጋር ሲነፃፀር የዜጎች የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ ከአራት ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርትና በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሌሎች አገራት የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያው ዝቅተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ዶክተር አሚር እንደገለጹት በ2006 ዓ.ም በተካሄደው ተመሳሳይ ጥናት የአገሪቱ አጠቃላይ የጤና ወጪ 49 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን ከሶስት ዓመት በኋላ ግን ወደ 71 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር አድጓል። ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ አጠቃላይ አገራዊው የጤና ወጪ እያደገ የመጣ ቢሆንም አሁን ካለው የህዝብ ብዛት፣ የጤና አገልግሎት ሁኔታና ፍላጎት አኳያ በቂ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ዓመታዊ በጀቷ ስምንት በመቶውን ለጤናው ዘርፍ እንደምትመድብም እንዲሁ ገልጸዋል። ይህም ቢሆን የዓለም ጤና ድርጅት የአገራትን የጤና በጀት አስመልክቶ ካስቀመጠው መስፈርት ሰባት በመቶ ያነሰ ነው ብለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት በማጠናከር የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን ያሟላ ይሆን ዘንድ መንግስት ለዘርፉ የሚመደበውን በጀት ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ሚኒስቴሩ አሳስበዋል። የዚህ ዓይነቱ ጥናት የጤና አገልግሎትን ለመላው ዜጋ ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ለማገዝና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚያስችል ግብአት ይሆናል።