ቀጥታ፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡትን አዲስ ተማሪዎች በፍኖተ ካርታው መሰረት ለማስተማር መዘጋጀቱን ገለፀ።

አዲስ አበባ መስከረም 7/2012 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2012 የሚቀበላቸውን አዳዲስ ተማሪዎች በፍኖተ ካርታው መሰረት የፍሬሽ ማን ኮርሶችን ለማስተማር መዘጋጀቱን ገለፀ። ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ለመጀመርም ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ሰባት ካምፓሶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ሁለት ኢንስቲትዩቶች በስሩ አሉት። ዩኒቨርሲቲው በ94 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 107 የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም በ 22 የፒ.ኤች.ዲ የትምህርት መርሃ ግብሮችና በ6 የህክምና ስፔሻሊቲ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፤ ከ42 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝም ታውቋል። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ አመታት የመማር ማስተማር ተግባርን ሲከውን የነበረ ሲሆን በተለይም በ2012 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን እየሰራ ነው። በትምህርት ዘመኑ ዩኒቨርሲቲውን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎች በፍኖተ ካርታው መሰረት የፍሬሽ ማን ኮርስ እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት። ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በማስተርስና ፒ.ኤች.ዲ ዲግሪ 17 አዳዲስ መርሃ ግብሮች ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልፀዋል። በአዲሱ የትምህርት ዘመን ሶስት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለት የፒ.ኤች.ዲ እና 12 የማስተርስ ዲግሪ አዳዲስ መርሃ ግብሮች ናቸው የተካተቱት። መርሃ ግብሮቹ በገበያው ፍላጎት የተመሰረቱና በቂ የመማሪያ ግብዓትና መምህራን መኖራቸው ተረጋግጦ የተከፈቱ መሆናቸውን በመግለፅ። መርሃ ግብሮቹ ስርዓተ ትምህርታቸው የፀደቀና የሰው ኃይል የተሟላላቸው በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ተማሪዎችን በመቀበል ትምህርቱ እንደሚጀመርም ነው ያስታወቁት። ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ በተጨማሪ በጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። እነዚህ ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም