በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ባለሀብቶች በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል - ዶክተር ማርቆስ ተክሌ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ባለሀብቶች በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል - ዶክተር ማርቆስ ተክሌ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2012 አፍሪካውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ከምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ /ኮሜሳ/ መስራች አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እና በቅርቡ የተቀላቀለችው ቱኒዚያ በመካከለቸው ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው። በምክክራቸውም ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችም የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ወደ አፍሪካ አገሮች በማዞር የአህጉሪቱን የእርስ በርስ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ማሳደግ እንዳለባቸው ተወስቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዓለም ገበያን መሳብ የሚችል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገች ነው። ለአብነትም በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩት ኢትዮ-ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ አየር መንገድ፣ ስኳር ፕሮጀክትና ሌሎች ተቋማትን ወደግል ለማዞር እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የንግድ ተቋማትን ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል የማዛወር ሂደቱ የአፍሪካን ብሎም ዓለምን ትኩረት መሳቡንም ገልጸዋል ሚኒስትር ዴኤታው። በመሆኑም ትኩረታቸውን ወደ አውሮፓና አሜሪካ አድርገው የቆዩት አፍሪካውያን ድርጅቶች ወደ ራሳቸው በማየት የአፍሪካን የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ማሳደግ አለባቸው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች እንደ ቱኒዚያ ካሉ መካከለኛ ገቢ ካላቸው የአፍሪካ አገሮች ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በመፍጠር በቀላሉ ውጤታማ መሆን ይችላሉም ብለዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ወደ አፍሪካ እንዳያተኩሩ ያገዳቸው ነገር የለም ብለዋል። ነገር ግን የምርት ጥራትና የተሻለ ካፖታል ያላቸው የአውሮፓና አሜሪካ ድርጅቶች ናቸው በሚል እሳቤ አፍሪካን ወደ ጎን ትተዋታል ብለዋል። በመሆኑም በቀጣይ "በአፍሪካ የተመረቱ የአፍሪካ መለያ ምርቶች" አንዲኖሩን በጋራ ለመስራት ከአፍሪካውያን ድርጅቶች ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል። የቱኒዚያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሀተም ፈርጃኒ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና ቱኒዚያ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ቱኒዚያ በቱሪዝም ዘርፍ ከኢትዮጵያ የተሻለ ልምድ እንዳላት ገልጸው፤ በዘርፉ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉም አውስተዋል። በማዕድን፣ በትራንስፖረት፣ በቱሪዝም፣ በመድሃኒት፣ በትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማት ዘርፎችም ለመስራት ጠንካራ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል። የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የአፍሪካን የንግድ ቀጠና ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል።