በምርት ዘመኑ የተሻለ የሰሊጥ ምርት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በምርት ዘመኑ የተሻለ የሰሊጥ ምርት ይጠበቃል
መስከረም 7/2012 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተክለማሪያም ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2011/2012 የምርት ዘመን በዞኑ ከ277 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል ተሸፍኗል፡፡ በሰሊጥ የተሸፈነው መሬት ባለፈው አመት ከለማው ጋር ሲነጻጸር በ9 ሺህ ሄክታር መሬት ያነሰ ቢሆንም የሰብሉ እድገትና ፍሬ አያያዙ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የመስክ ግምገማም በምርት ዘመኑ በሰሊጥ ሰብል ከተሸፈነው ማሳ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የምርት መጠን ባለፈው ዓመት ከተገኘው በግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ ከሁመራ እርሻ ምርምር ማእከል በምርምር የወጡ የሰሊጥ ምርጥ ዝርያዎች ጥቅም ላይ መዋል የወቅቱ የዝናብ ስርጭትና መጠን ለልማቱ ተስማሚ መሆን ጋር ተዳምሮ ለምርታማነት መጨመር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ በዚህም ባለፈው አመት በሄክታር 3 ነጥብ 6 የነበረው የሰሊጥ ምርታማነት ዘንድሮ ወደ ስድስት ኩንታል ያድጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በቃፍታ ሁመራ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አቶ ሃይለ ወልደ ደሚካኤል በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ 50 ሄክታር መሬት በምርጥ የሰሊጥ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል፡፡ ምርጥ ዘር ከመጠቀማቸው በተጨማሪ የዝናቡ ስርጭትና መጠን ለሰብሉ ተስማሚ መሆኑን ተከትሎ ሰብሉ ካለፈው ዓመት የተሻለ ቁመና እንዲኖረውና ፍሬ እንዲይዝ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ 20 ሄክታር መሬት ሰሊጥ ማልማታቸውን የተናገሩት ደግሞ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የትርካን ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሶ አደር ድያቆን አለምብርሃን ገብረ ገርግሰ ናቸው፡ ዘንድሮ ዝናብ የበዛበት ቢሆንም በፍሬ አያያዙ ጥሩ በመሆኑ ከአንድ ሄክታር መሬት ከአራት ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።