የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች ብቻ የቀሩት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በፕሪሚየር ሊጉ ከመሪው ጅማ አባጅፋር ጋር እኩል 45 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ 11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከደደቢት ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። የሊጉ መሪ ጅማ አባጅፋር ከሜዳው ውጭ ወልዲያ ከተማን ነገ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገጥማል። በክልል ከተሞች በነገው ዕለት ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ከሲዳማ ቡና ረፋድ 4 ሰዓት፣ መቐለ ላይ መቐሌ ከተማ ከመከላከያ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬድዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 9 ሰዓት ይገናኛሉ። ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ሀዋሳ ከተማን የሚገጥም ሲሆን አርባምንጭ ከተማ በሜዳው አዳማ ከተማን ያስተናግዳል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊና ወራጅ ክለቦች እስካሁን ባለመለየታቸው የሊጉ ፉክክር አጓጊ ሆኗል። በተለይም የሊጉ አሸናፊ ለመሆን ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው የሚፎካከሩ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ከሶስት ያልበለጠ በመሆኑ ፉክክሩን በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ሊጉን ጅማ አባጅፋር በ45 ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ነጥብ በጎል ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ከተማ ደግሞ በ43 ነጥብና በተመሳሳይ የጎል መጠን ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ አዳማ ከተማ በ42 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። በሊጉ የወራጅ ቀጠና ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ28 ነጥብ 14ኛ ደረጃ፣ አርባምንጭ ከተማ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በ27 ነጥብ 15ኛ እንዲሁም ወልዲያ ከተማ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ በሊጉ ግርጌ ተቀምጠዋል።