ታላቁ የኢሬቻ የጎዳና ሩጫ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል

47
መስከረም 07/2012 ታላቁ "የሆራ ፊንፊኔ" የኢሬቻ ሩጫ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። ሩጫው መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚካሄድ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዘም ቢሮ ከ'ዲሲቲ ኢንተርቴይማንት' ጋር በመሆን እንደሚያዘጋጁ ተገልጿል። በዚህ የሩጫ ውድድር ላይም ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋቅጋሪ ለኢዜአ ተናግረዋል። እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ የሩጫው ቲ-ሸርት በፌዴራልና በክልሉ በመሰራጨት ላይ ያለ ሲሆን ሽያጩም እየተካሄደ ይገኛል። የአንድ ቲ-ሸርት ዋጋ 250 ብር ሲሆን የመሸጫ ቦታዎች በፌዴራልና በክልሉ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰራተኞች እንዲሁም በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞንና በአዲስ አበባ የሚገኙ ነዋሪዎች ከኦሮሞ ባህል ማዕከል ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል። በክልሉ ሌሎች ዞኖች የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ በዞን እና በወረዳ እንዲሁም በሁሉም ከተሞች ባሉት የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም