የሰሊጥ ኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው - አምራች አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የሰሊጥ ኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው - አምራች አርሶ አደሮች
መስከረም 07/2012 ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለውጪ ገበያ በሚቀርበው ሰሊጥ ምርታማነትና ጥራት ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የማእከላዊ ጎንደር ዞን ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ያዘጋጀው የመስክ ጉብኝት በዞኑ በታች አርማጭሆና ጠገዴ ወረዳዎች ትናንት ተካሂዷል፡፡ በወረዳዎቹ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ አምና በሰርቶ ማሳያና በተመረጡ አርሶ አደሮች ማሳ በተካሄደ የሙከራ ስራ የሰሊጥ ምርታማነትን በሄክታር ከ4 ወደ 8 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል፡፡ በታች አርማጭሆ ወረዳ የኪሻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አድኖ ሙላት እንደተናገሩት በ2011/12 ምርት ዘመን የሰሊጥ እርሻን ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም የአስተራራስ ዘዴ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አምና በሙከራ ደረጃ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ያደረጉ የወረዳው አርሶአደሮች ሰሊጥን በሄክታር የ3 ኩንታል ጭማሪ በማግኘታቸው መነሳሳት እንደፈጠረባቸውም ገልፀዋል። የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ታረቀኝ ሞላ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ሰሊጥን በብተና ካልሆነ በስተቀር በመስመር አንዘራም፤ ግብአትም አንጠቀምም ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ምርምር ማእከሉ አምና ባደረገልኝ የሙያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ድጋፍ ሰሊጥን በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ዘርቼ ጥራት ያለው ምርት ማምረት አስችሎኛል በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆኛለሁ ብለዋል፡፡ ''ኩታ ገጠም የሰሊጥ እርሻ በጋራ ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ለማረም፣ ግብአት ለመጠቀምና ምርቱንም በወቅቱ ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮአል'' ያሉት በጠገዴ ወረዳ የማርዘነብ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ታርቆ ሙሉአለም ናቸው። ''በዘንድሮ ክረምት ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም 3 ሄክታር የእርሻ መሬቴን 10 ከሚሆኑ አጎራባች አርሶአደሮች ጋር ሰሊጥ ዘርቻለሁ'' ብለዋል፡፡ ''አምና ከዚሁ መሬት ቴክኖሎጂውን ሳልጠቀም 12 ኩንታል ሰሊጥ አግኝቼ ነበር'' ያሉት አርሶ አደሩ ዘንድሮ ግን ምርታማነትን በእጥፍ አሳድጋለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የጠገዴ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘውዱ ጀጃው በበኩላቸው በወረዳው አምና በሙከራ ደረጃ በተካሄደው የሰሊጥ ኩታ ገጠም እርሻ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 4 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በ2011/12 ምርት ዘመን ተሞክሮውን በማስፋት 14ሺ ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮችንና 130 የእርሻ ባለሀብቶችን በማሳተፍ 28ሺ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በሰሊጥ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ በምርት ዘመኑ 224ሺ ኩንታል የሰሊጥ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ምርቱም ከአምናው በ112ሺ ኩንታል ጭማሪ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ የነበሩት ዶክተር ቦሰና ተገኘ በበኩላቸው ኩታ ገጠም የእርሻ ቴክኖሎጂ በክልሉ በምርት ጭማሪ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ይህን ተሞክሮ በማስፋት በኩል ከአርሶአደሩ ጀምሮ የግብርና ባለሙያዎችና የምርምር ማእከላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የጎንደር ግብር ምርምር ማእከል ዳይሬክተር አቶ አስፋው አዛናው በሄክታር እስከ 10 ኩንታል ምርት የሚሰጡ አባ ሲና እና ጎንደር 1 የተባሉ ምርጥ የሰሊጥ ዝርያዎችን ማእከሉ ለአርሶ አደሩ ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ 8 ሰሊጥ አብቃይ ወረዎች በምርት ዘመኑ 62ሺ ሄክታር መሬት በሰሊጥ የተሸፈነ ሲሆን ከ533ሺ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም አብራርተዋል። በመስክ ጉብኝቱ ላይ የክልልና የዞን አመራሮችን ጨምሮ ተመራማሪዎች፣ አርሶአደሮችና የግብርና ባለሙዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡