በነገሌ ከተማ ወላጆቻቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ህጻናት ድጋፍ ተደረገ

65
ነገሌ ኢዜአ መስከረም 7/2012 የነገሌ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ለአንድ ሺህ 500 ህጻናት የትምህርት መርጃ ቁሰቀቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ታምሩ ታዬ እንዳሉት በተያዘው የትምህርት ዘመን በከተማው በሚገኙ ስምንት ትምህርት ቤቶች 3 ሺ 100 አዲስ ገቢ ህጻናት መደበኛ ትምህርት ለመከታተል ተመዝግበዋል፡፡ መደበኛ ትምህርቱን ለመከታተል አዲስ ከተመዘገቡ ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የህጻናቱን የትምህርት ተሳትፎ ለማበረታታት 6 ሺ 400 ደብተር፣ 2 ሺህ እርሳስና እስኪርብቶ በስጦታ መበርከቱን ገልጸዋል፡፡ ጽህፈት ቤቱ ለህጻናቱ በስጦታ ያበረከተው የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በ112 ሺህ ብር ወጪ የተገዛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ስጦታውን ያበረከቱት የጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ነጋሽ ቡላላ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በነገሌ ከተማ እስካሁን 12 ሺ አዲስና ነባር መደበኛ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ በነገሌ ከተማ በሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች የአዲሱን አመት የትምህርት ስራ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡ በጉጂ ዞንም በዚህ አመት ከ514 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም