ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች አሏቸው

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 6/2011ኢትዮጵያና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ቱሪዝምንና ሪልስቴትን ጨምሮ በትብብር የሚሰሩባቸው በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዳሏቸው የዱባይ የንግድ ምክር ቤት አስታወቀ። በኢትዮጵያ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ኤምባሲ ከዱባይ የንግድ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የሁለት ቀናት የንግድ ሲፖዚየም ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በዚሁ ወቅት በዱባይ የንግድ ምክር ቤት የአለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ኦማር አብዱላዚዝ እንዳሉት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል ማጥናትና በዱባይና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ማጠናከር የዚምፖዚየሙ ዓላማ ነው። በአፍሪካ የመጀመሪያው የዱባይ የንግድ ምክር ቤት ቅርንጫፍ ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መከፈቱን ያነሱት ሚስተር ኦማር አብዱላዚዝ ሁለቱ አገራት በትብብር ሊሰሯቸው የሚችሉ በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች አሏቸው ብለዋል። በተለይም ቱሪዝምና ሪልስቴት በጋራ መስራት የሚቻልባቸው ሰፊ እድሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሲምፖዚየሙ ሲጀመር የንግድና ኢንደስትሪ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ባደረጉት ንግግር ከመካከለኛ ምስራቅ አገራት መካከል ዋነኛ የኢትዮጵያ የንግድ ሸሪክ ከሆነችው የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ጋር ያለው የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ባለኃብቶች በመድሃኒት፣ በቀላል ማምረቻና በሌሎች ዘርፎች በኢትዮጵያ መሰማራታቸውን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታው አገሪቱ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መዳረሻ መሆኗንም ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያና በአገሪቱ መካከል ያለውን ይህንን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የኢንቨስትመንት ጥበቃና የማስተዋወቅ ስምምነት መደረጉንም አክለዋል። በኢትዮጵያና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ለማመጣጠንም የተለያዩ ሥራዎች ይከናወናሉም ብለዋል። የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በማምረት ምርቶቻቸውን ወደተለያዩ የውጭ አገራት የሚልኩበትን መንገድ ለማመቻቸት መንግስት እንደሚሰራም ተናግረዋል። የአገሪቱን የወደብ አጠቃቀምና ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን የትራንስፖርት ትስስር ለማሻሻልም እንዲሁ። የዱባይ የንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ተዋበች ኃይሉ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶችና ከኢትዮጰያ ወደ ዱባይ በሚላኩ ምርቶች መጠን መካከል ሰፊ ልዩነት  መኖሩን ይናገራሉ። ይህንንም ያልተመጣጠነ የንግድ ሚዛን ለማሻሻል ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ወደኢምሬት ለመላክ የሚያስችል ተግባር ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም ሴት የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች  ምርቶቻቸውን ወደ ዱባይ የሚልኩባቸውን መንገዶች ለማመቻቸትና ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ምክትል ኮሚሽነር ሀና አርአያ ስላሴ መንግስት በአገሪቱ ያለውን የስራ ሁኔታ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ይከናወናሉ ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ማጠናከርም በዘርፉ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት መካከል ናቸው ብለዋል። ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት መጠንና ጥራት ማሳደግ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሚፈለገው መጠን መሳብ በመንግስት ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም