ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሱዳን በቱሪዝም ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ትስስር እያበጁ ነው

መስከረም 6/2012 ኢትዮጵያና ሱዳን በቱሪዝሙ ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የሁለቱንም አገራት የቱሪስት መዳረሻዎች መሰረት ያደረገ አሰራር እየዘረጉ መሆኑ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር እና አስር የሱዳን ተዋቂ አስጎብኝዎች ዛሬ በአዲስ አበባ መክረዋል። በውይይቱም ሁለቱ ጎረቤት አገራት ከጥንት ጀምሮ የሚያስተሳስራቸውን የጋራ ባህልና እሴት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲያስችል በአገራቱ መካከል የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተነስቷል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ ሁለቱ ጎረቤት አገራት በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏቸው ሲሆን የአሁኑ እንቅስቃሴም በጋራ የቱሪዝም የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ እንደተጀመረ ገልጸዋል። በመሆኑም ላለፉት እስር ቀናት የሱዳን የአስጎብኚ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ይህም ሁለቱም አገራት ያላቸውን የቱሩዝም መዳረሻ በማስተያየት በጋራ ለመስራት መንገድ እንደሚከፍት አንስተዋል። ከሱዳን አስጎብኚዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አብረሃም አለሙ እንዳሉት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ከሚደረጉ የቱሪዝም ጉብኝቶች ባሻገር ከሌሎች አገራት የሚመጡ ቱሪስቶች ሲኖሩም በጋራ ለመስራት  የሚያስችል አሰራር እንደሚፈጠር ገልጸዋል። የኢትዮጵያ  አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ በበኩላቸው ቱሪዝም ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ፤ ሁለቱ አገራት ከሌሎች አገር ጎብኚዎች  ጋር ለመስራት  መነሳታቸው  ቱሪስቶችን በቀጠናው ላይ ቆይታቸው አንዲራዘም ከማድረግ አኳያ ሚናው ላቅ ያለ ነው ብለዋል። በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቱሪዝም ፕሮሞሽን ኦፊሰር አቶ ሳዲክ መሃዲ ዩሱፍ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር ለማስተዋወቅ እንዲህ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የቱሪዝም የገበያ ትስስር ለመፍጠርና አገራቱን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋርም በቀጣይነት የሚሰራበት ነው ብለዋል። የሱዳን አስጎኚዎች በኢትዮጵያ በመዘዋወር የአልነጃሺን መስጊድ፣ የሀረርን ግንብ፣ ባህር ዳርና አካባቢዋን እንዲሁም ሌሎች በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የጎበኙ ሲሆን ጉብኝቱም በሱዳን መገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንደተሰጠው  ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም