ቀጥታ፡

የአቬሽን ኢንዱስትሪ ደህንነት ፈተናዎችን ለመቋቋም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል

መስከረም 6/2012 በዓለም አቀፍ የአየር በረራ ስርዓት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ ባለ ድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተነገረ። በበረራ ደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመክር የሶስት ቀናት ስብሰባ በዓለም አቀፉ የአብራሪዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ስብሰባውን በይፋ የከፈቱት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዳሉት ፤ ብሄራዊ ዓርማ አዝሎ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አቬሽን ኢንዱስትሪ ኩራት ሆኖ በእድገት ጎዳና የተራመደው ከመንግስት በሚደረግለት ድጋፍና ክትትል ነው። 'የበረራ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው' ያሉት ሚኒስትሯ በላቀ ደረጃ ቀጣይነት ያለው የአቬሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ሁሉንም የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ትብብር ይጠይቃል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ አቬሽን ኢንዱስትሪ የደህንነትን ጉዳይ ቀዳሚ የትኩረት ማዕከል ማድረጉ በመላው ዓለም አስተማማኝ ምልክት መፍጠሩን ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት ዕውን መሆን ባለድርሻ አካላት ላለፉት ዓመታት ያደረጉት ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተዋል። በፌዴሬሽኑ የምስራቅና የአፍሪካ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ሳውሃኤል ዳለል በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ደህንነቱ የተጠበቀ የበረራ ስርዓት ለመገንባት የአብራሪዎች፣ የአምራቾች፣ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ አየር መንገዶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት ግድ ይላቸዋል ብለዋል። የአየር ንብረት ሁኔታ፣ የሳይበር ጥቃት፣ ግጭትና ተወዳዳሪነትን የአቬሽን ኢንዱስትሪው ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች መካከል ጠቅሰዋል። ዓለም በደረሰችበት የአቬሽን ኢንዱስትሪ ውስብስብነትና የፍላጎት ማሻቀብ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በቴክኖሎጂና በሙያ ስልጡን ሙያተኛ መገንባት ይሻል ነው ያሉት። ከመቶ በላይ በሆኑ አገራት ከ100 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የዓለም አቀፉ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበራት ፌዴሬሽንም በአዲስ አበባ በሚያደርገው የቀጣናው ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ይመክራል። የኢትዮጵያ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን የአቬሽን ኢንዱስትሪው እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው የደህንነት ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ሲታይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት እያደገ ያለ ተቋም መሆኑን ገልፀው፤ ነገር ግን ኢንዱስትሪውን በደንብ መከታተልና መቆጣጠር የሚችለው የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን እኩል ማደግ እንዳለበት አመልክተዋል። መንግስትም ተቋሙን ከአየር መንገዱ ጋር እኩል የሚራመድ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለበትም ሃሳብ ሰንዝረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም