ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኢንዶኔዥያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

መስከረም 6/2012 የኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ የንግድ ልውውጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተሻሻለ መምጣቱን በኢትዮጵያ በጅቡቲና በአፍሪካ ህብረት የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር ገለጹ። የኢትዮ-ኢንዶኔዥያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ በጅቡቲና በአፍሪካ ህብረት የአገሪቷ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር ገለጹ። የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። አገራቱ በተለይም በንግድና አንቨስትመንት ዘርፎች የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ባይሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የንግድ መጠናቸው እየተሻሻለ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ አምስት የአገራቸው ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ፣ በግብርና ማቀነባበርና በሳሙና ማምረት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸውን አምባሳደር አል ቡሲራ አስታውሰዋል። ከእነዚህ ወስጥም ሁለቱ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እያመረቱ መሆናቸውን በመግለጽ። በሚቀጥለው ጥቅምት ወር 25 የሚሆኑ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ልዑካን አባላት ወደ ኢንዶኔዥያ ጃካርታ በሚዘጋጀው የንግድ ኤክስፖ ላይ አንዲሳተፉ ኤምባሲው ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ ከኤክስፖው በኋላ የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ እንደሚያጠኑ ነው አምባሳደሩ ያመለከቱት። አገራቱ ከንግድና ኢንቨስትመንት ባለፈ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ያስታወቁት አምባሳደሩ፣ በተለይ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ትብብር እየፈጠሩ ነው ብለዋል። ባህር ዳር፣ ወሎና ሀዋሳ ዩኒቨርስቲዎች ኢንዶኔዥያ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ትሰስር በመፍጠር በጋራ እየሰሩ እንደሆነም ነው ያብራሩት። ኢንዶኔዥያ በሚቀጥለው ዓመት ለ100 ኢትዮጵያውያን በነርሲንግ የትምህርት ዕድል እንደምትሰጥም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል። ሁለቱ አገሮች በግብርና፣ በትምህርት፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ፣ በአካባቢ ጥበቃና በጤና ዘርፎች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከግብርና ምርቶችን በዋነኛነት ቡናን ወደ ኢንዶኔዥያ የምትልክ ሲሆን የጽህፈት መሳሪያዎችን፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የጽዳት ምርቶች፣ የምግብና መጠጥ ምርቶችን ከኢንዶኔዥያ ታስገባለች። እኤአ በ2007 የአገራቱ የንግድ ልውውጥ መጠን 69 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የነበረ ሲሆን በ2017 ወደ 293 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም