ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ታሪክ እንዳላቸው መገንዘብ ይገባል - ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 6/2012 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ታሪክ እንዳላቸው መገንዘብ እንደሚገባ ገለጹ። የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር መዋቅራዊ በመሆኑ ይህንን መፍታት ይገባል ሲሉ አቶ ልደቱ አያሌው ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ባህሩ ''ኢትዮያጵዊያን አንድነታቸውን የሚያጠናክር የጋራ ታሪክ ቢኖራቸውም አልተሰራበትም'' ባይ ናቸው። ወጣቶች ታሪክን ከማወቅ ይልቅ ወደፖለቲካዊ ስሜት ብቻ እየሄዱ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከሚያጋጥማት ችግር አንዱ ለታሪክ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት ማነስ መሆኑን አንሰተዋል። የታሪክ ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መቋረጡም ትልቅ ስህተት እንደነበር አብራርተዋል። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተማሪዎች መደበኛ ኮርስ መውሰድ ከመጀመራቸው በፊት የአገራቸውን ታሪክ፣ ጂኦግራፊና ባህል መማር የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አስገንዝበዋል። ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በአገራዊ አንድነት ላይ የሚነሳው ችግር መዋቅራዊ ችግር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ያስገነዝባሉ። ''መዋቅራዊ ችግር በመዋቅራዊ መፍትሄ ነው የሚፈታው'' ያሉት አቶ ልደቱ፤ መሰረታዊ ቅራኔዎች ለመፍታት የሚያስችል ውይይት መካሄድ እንዳለበት ገልጸዋል። የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ በአብሮነትና አገራዊ አንድነት ላይ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ከስሜት ሰክኖ በቅድሚያ ችግሮችን እንዴት መሻገር እንደሚቻል ማሰብ እንዳለለበት ይመክራሉ። አቶ ልደቱ በበኩላቸው ላለፉት 27 ዓመታት ፖለቲካ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔርና ልዩነት ተኮር ሆኖ ሲሰራ መቆየቱ ለውጥ እንዲመጣ ማስገደዱን ያስታውሳሉ። መዋቅራዊ አደረጃጀትን በመፈተሽ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ''አንድ አገር መሰረታዊ ልዩነት ይዞ ወደ ምርጫ ከሄደ የፖሊሲ ውይይት ሊያደርግ አይችልም'' ብለዋል። የሰብዓዊ መብት ተማጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ድንቅ አገራዊ እሴቶች እንደነበሩ ገልጸው፣ ኢትዮጵያዊያን በህግ አምላክ በመባባል ብቻ ግጭትን ሲያስወግዱ፣ ሰላምን ሲያስፍኑ እንደነበር አውስተዋል። አቶ ኦባንግ ግለሰቦች ወንጀል ሰርተው ብሔርን መሸሸጊያ የማድረግ ሁኔታ ጎጂ እንደሆነም አስገንዝበዋል። ሰው በአብሮነት የሚኖር ማህበራዊ ፍጡር መሆኑን የገለጹት አቶ ኦባንግ፤ መለያየትን ከሚያራምድ አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነትና አብሮነት ላይ በማተኮር መልካም እሴቶችን ለትውልድ ማውረስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም