ቱኒዚያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ፍላጎት አሳየች

69
መስከረም 6/2012 ቱኒዚያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ፍላጎት እንዳላት ገለጸች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ የቱኒዚያ አቻቸውን ሚስተር ሐቲም ፈርጃኒን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ አገሮች በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ስድስተኛውን የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን በቱኒዝ አካሂደው ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሴቶችና ህጻናት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ እንደገለጹት፤ ቱኒዚያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ፍላጎት አላት። ቱኒዝያ በዓመት ዘጠኝ ሚሊዮን ጎብኚዎች ወደ አገሯ የሚገቡ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን አስር እጥፍ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ቱኒዝያ በአፍሪካ ኀብረት ጉዳዮች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ወይዘሮ ሒሩት፤ ቱኒዝያ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት አባል በመሆን የምትመረጠው ቱኒዝያ ከኢትዮጵያ ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል። የቱኒዝያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ሐቲም ፈርጃኒ በበኩላቸው ቱኒዝያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን አቅም ለኢትዮጵያ ለማካፈል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በአምስት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም አብራርተዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ ተናግረዋል። የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር አርባ የቱኒዝያ የንግድ ልዑካን ቡድን ነገ መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት እንደሚያካሂድ ሚስተር ፈርጃኒ ተናግረዋል። ''ቱኒዝያ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት ሁለቱ አገሮች በአፍሪካና በዓለም ገበያ ውስጥ በጋራ ለመስራት ይችላሉ'' ብለዋል። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከውጪ ጉዳይ ሚኒስተር እና ከቱኒዝያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው ኢትዮ- ቱኒዝያ የቢዝነስ ፎረም መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር። የፎረሙ ዋና ዓላማ በሁለቱ አገሮች ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና አዳዲስ የቢዝነስ አጋርነት ለመፍጠር እንደነበረ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም