ኬንያ የሞያሌን መንገድ ዘግታለች የሚለው መረጃ ሐሰት ነው - አምባሳደር መለስ ዓለም

99

መስከረም 5/2012 ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናት የሞያሌ መንገድ ዘግታለች የሚለው መረጃ ውሸት መሆኑን በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።

የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በሞያሌ መንገድ እየተስፋፋ ባለው ህገ-ወጥ ንግድ ምክንያት ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን የሞያሌ መንገድ ዘግታለች በማለት በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።

ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም "ምንም የተዘጋ መንገድም ድንበርም የለም፤  እየተሰራጩ ያሉት መረጃዎች ውሸት እና መሰረተ ቢስ ናቸው" በማለት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸውና በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በጸጥታ እና በንግድ የሚመክሩባቸው የጋራ መድረኮች እንዳሏቸውም ተናግረዋል።

የንግድ ጉዳይንም በተመለከተ አገራቱ በተለያዩ ጊዜያት ምክክር እያደረጉ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ ዜጎች በሞያሌ ድንበር በኩል አድርገው ወደ ኬንያ መግባት እንደሚችሉና የሞያሌ መንገድ ተዘጋ የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም