ለኢጋድ አባል አገራት የሚያገለግል የካንሰር የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢጋድ አባል አገራት የሚያገለግል የካንሰር የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው
መስከረም 5/2012 ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል የሚያገለግል የካንሰር የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው። በአዲስ አበባ በ450 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ይኽንን ማዕከል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ትልቁን ድርሻ የግንባታውን የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢጋድ የጤና ሚኒስትሮች ሰብሳቢ ዶክተር አሚር አማን ገልጸዋል። ማዕከሉ እንዲገነባ የተፈለገውም በኢጋድ አባል አገራት የካንሰር ህሙማን ቁጥጥርና ለበሽታው ተጋላጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነም አክለዋል። ዶክተር አሚን ካንሰርን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎችም እጥረት መኖሩን ጠቁመው ለአብነትም በዘርፉ የሰለጠኑት የጤና ባለሙያዎች ቁጥር በአፍሪካ ከ2 ሺ እንደማይበልጡም ተናግረዋል። እነዚህም የጤና ባለሙያዎች አብዛኞቹ በደቡብ አፍሪካና በግብጽ እንደሚገኙና በኢጋድ አባል አገራት አከባቢ የባለሙያ እጥረት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት። አሁን ላይም 260 ሚሊዮን ሕዝብ በሚገኝበት ምስራቅ አፍሪካ፤ አንድ የካንሰር ሃኪም በአማካይ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ማሳያም አቅርበዋል። ጎን ለጎንም በአከባቢው አገራት የሚሰጠው የካንሰር ህክምና በተበጣጠሰ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ይህንንም አንድ ወጥ ለማድረግ ማዕከሉ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። በማዕከሉም የአከባቢው አገራት ሕዝቦች የጤና አገልገሎት በማግኘት እንዲሁም መንግሥታት ደግሞ በዘርፉ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላልም ነው ያሉት።