የብርጭቆ ወረቀት ፋብሪካው የተሸጠው “በሴራ” ወይስ “በኪሳራ”? - ኢዜአ አማርኛ
የብርጭቆ ወረቀት ፋብሪካው የተሸጠው “በሴራ” ወይስ “በኪሳራ”?
መስከረም 5/2012 ''የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባልሰጠኝ ብድር ባለእዳ አድርጎ ንብረቴን በግፍ ሸጠብኝ'' አቶ ዮናስ ብሩ ግለሰቡ ከባንኩ ጋር በገቡት ውል መሰረት ግዴታቸውን ባለመፈፀማቸው እርምጃ ወስጃለሁ - ባንኩ አቶ ዮናስ ብሩ ባደረጉት ምርምር በኢትዮጵያ የብርጭቆ ወረቀት፣ ከኮላ የሚዘጋጅ ማጣበቂያ፣ ግራይንዲንግ ዲስክና ናፒንግ ኮምፓነንት በመፍጠራቸው የባለቤትነት መብት ተሰጥቷቸዋል። በተለያዩ ዓመታት ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ያገኟቸው የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀቶችም አሏቸው። በተለይ ለእንጨትና ብረታብረት ማለስለሻነት የሚያገለግለው የብርጭቆ ወረቀት ፈጠራቸው በ1998 ዓ.ም ከዓለም ባንክ የ15 ሺህ ዶላር ተሸላሚ አድርጓቸዋል። በዚህም በሰበታ ከተማ በ6 ሺህ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በገነቡት ፋብሪካ በቀን ከ100 ጥቅል በላይ የብርጭቆ ወረቀት ማምረት ችለዋል። ከቻይና እና ጀርመን ወደ አገር ውስጥ እየገባ በቅደም ተከተል በ30 እና 120 ብር ይሸጥ የነበረውን የብርጭቆ ወረቀት ግዥ በማስቀረት አንዱን በ15 ብር ለገበያ ያቀርባል። በዚህም ፋብሪካው ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ ወጪ ታስገባ የነበረውን የብርጭቆ ወረቀት በአገር ውስጥ ምርት መተካት የቻለ ሲሆን ለ60 ዜጎችም የስራ እድል ፈጥሯል። ፋብሪካው ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለውም አቶ ዮናስ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ፋብሪካው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያልተገባ አሰራር ችግር ገጥሞት ላለፉት አምስት ወራት ስራ ለማቆም መገደዱን ይናገራሉ። ባንኩ ለፋብሪካው ስራ ማስኬጃ ብድር ፈቅዶ 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ሚያዚያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም ከአቶ ዮናስ ጋር ውል ፈፅሞ ነበር። በብድር ስምምነቱ አንቀፅ 3 መሰረት የብድሩ ዓላማ ተብሎ የተቀመጠው ተበዳሪው ብድሩን የሚያውለው ለስራ ማስኬጃ አላማ ብቻ ነው። ባንኩ ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም ለተበዳሪው በፃፈው ደብዳቤ መሰረት አሁን ላይ 1 ሚሊዮን 913 ሺህ ብር ለተበዳሪው የተለቀቀላቸው ቢሆንም ክፍያው የተፃፈው ለአቅራቢ ድርጅት መሆኑን ይገልፃል። ሆኖም ከተለቀቀው ገንዘብ ውስጥ 113 ሺህ ብር ብቻ ለሰራተኛ ክፍያ እንዲውል ወደ አቶ ዮናስ አካውንት ገቢ መደረጉን ጠቅሶ ቀሪው ብር ከውጭ ለሚገባው ማሽን ክፍያ እንዲሁም የስራው ሁኔታ ታይቶ የሚለቀቅ ነበር። አቶ ዮናስ እንደሚሉት፤ ለጥሬ እቃ አቅራቢዎች ተከፍሎ ለፋብሪካው የግብአት አቅርቦት ይውላል በተባለው መሰረት በሶስተኛ ወገን ገቢ የተደረገላቸው ነገር የለም። በመሆኑም አቶ ዮናስ ከባንኩ ጋር በገቡት ውል መሰረት የተፈቀደላቸው ብድር ገቢ ሳይሆንና በሶስተኛ ወገን ተገዝቶ ገቢ የተደረገላቸው የምርት ግብአት ሳይኖር ብድር እንዲከፍሉ መጠየቁ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ይህ ሁሉ ሳይፈፀም ቆይቶ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት እየተስተጓጎለ ባለበት አጋጣሚ ባንኩ ፋብሪካውን ለመሸጥ ከአንድም ሁለት ጊዜ ጨረታ ማውጣቱ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በዚህም በሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ባንኩ በ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መነሻ ዋጋ ፋብሪካውን ለመሸጥ ለጨረታ አቅርቦት የነበረ ቢሆንም ባላወቁት ሁኔታ ተሰርዞ ነበር። ይሁንና ነሃሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ዳግም ጨረታ አውጥቶ በ5 ሚሊዮን ብር እንዲሸጥ አድርጎታል። “ከምርምር ስራዬ አንዱ የሆነውን ፍብሪካ ባንኩ በግፍ ሸጠብኝ፤ እዳ ለመክፈል ብጠይቅም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በ30 ቀናት ውስጥ መክፈል ይኖርብሃል ተብያለሁ፤ ይህም ፋብሪካውን ለመንጠቅ የታለመ ሴራ ነው” ይላሉ። ባንኩ በ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መነሻ ዋጋ ጨረታ አውጥቶ እርሳቸው ለመክፈል ሲጠይቁ ግን የተጋነነ ክፍያ መጠየቁም ተገቢ እንዳልሆነ ያምናሉ። “ይህም ባንኩ በፈጠራ ባለቤትነት መብቴ እንዳልሰራ ሆን ብሎ በደል እየፈፀመብኝ መሆኑን በግልፅ ያሳያል” ብለዋል። “ባንኩ ባልሰጠኝ ብድር እዳ እንዲከፍል መጠየቁም አሳዝኖኛል፤ በደል እየተፈፀመብኝ በመሆኑ ፍትህ እሻለሁ” ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስኪያጅ አቶ የአብስራ ከበደ እንደሚሉት፤ ቅሬታ አቅራቢው አቶ ዮናስ በብድር ሂደቱ ከባንኩ ጋር በገቡት ውል መሰረት ግዴታቸውን አልተወጡም። ለዚህም ባንኩ ያበደራቸውን ገንዘብ ለመክፈል የሰጣቸውን የእፎይታ ጊዜ ከስድስት ወር ወደ አንድ ዓመት አራዝሞላቸዋል። ''አቶ ዮናስ በገቡት ውል መሰረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ባንኩ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢያሳውቃቸውም መፈፀም አልቻሉም'' ብለዋል። ከብድሩም ባንኩ ለፋብሪካው ጥሬ እቃ አቅራቢ ድርጅቶች ቀጥታ ክፍያ የሚፈፅም መሆኑም ስምምነት የተደረገበት መሆኑን አቶ የአብስራ ገልጸዋል። ግለሰቡ ላቋቋሙት የብርጭቆ ወረቀት ፋብሪካ ባንኩ ከፈቀደላቸው 9 ነጥብ 914 ሚሊዮን ብር 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብሩ ለጥሬ እቃ ግዥ፣ 845 ሺህ 250 ብር ለማሽነሪ ግዥ፣ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ለተሽከርካሪ እና 149 ሺህ 709 ብሩ ለኢንሹራንስ፣ ደመወዝና ሌሎች ክፍያዎች የሚውል ተብሎ ተለይቷል። በዚህም መሰረት በእስካሁኑ ሂደት ከተፈቀደላቸው ብድር ውስጥ ባንኩ 6 ሚሊዮን 424 ሺህ 236 ብር ወጪ አድርጓል ተብሏል። ለዚህ ዘገባ ግብአት ማስረጃ ይሆነን ዘንድ የተባለው ብር መከፈሉን የሚያረጋግጥ ዶክመንት ባንኩን ጠይቀን ባይሰጠንም አቶ የአብስራ ግን ''ለመከፈሉ የተሟላ ማስረጃ አለ'' ብለዋል። በብድር ስምምነቱ አንቀፅ 5 ንኡስ ቁጥር 5.1 መሰረት ተበዳሪው በየወሩ በእለታዊ የብድር ገንዘብ መጠን በየዓመቱ 9 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ መክፈል ይጠበቅበታል። በአንቀፅ 7 መሰረትም ብድሩ ከልዩ ልዩ ወጪዎችና ከወለዱ ጋር ከጥር 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በየሶስት ወሩ 683 ሺህ 318 ብር የሚከፈል መሆኑም በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል። ሆኖም ተበዳሪው ከባንኩ ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት ግዴታቸውን መወጣት አለመቻላቸውን የባንኩ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። የብድር አመላለሱን ለማስተካከል ባንኩ ስላደረገላቸው ድጋፍና ቀጣይ መክፈል በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አቶ ዮናስ በ9/04/2011፣ በ20/02/2011 እንዲሁም በ01/02/2011 ዓ.ም ለባንኩ የፃፉትንም ደብዳቤ አቶ የአብስራ በማስረጃነት ጠቅሰዋል። ተበዳሪው በ01/02/2011 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤያቸው ባንኩ ላደረገላቸው ሙያዊ ምክርና እገዛ ምስጋናቸውን በማቅረብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የብድሩን 400 ሺህ ብር ለባንኩ ገቢ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። በ20/02/2011 ዓ.ም ደግሞ በ15 ቀናት ውስጥ የብድሩን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ለባንኩ ገቢ ለማድረግ ቃል ቢገቡም መፈጸም አለመቻላቸውን አቶ የአብስራ ገልጸዋል። በመሆኑም ባንኩ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ተጠቅሞ ግለሰቡ የወሰዱትን ብድር መክፈል ባለመቻላቸው ፋብሪካውን በጨረታ ለመሸጥ ባንኩ መገደዱን ተናግረዋል። ከባንኩ አሰራርና ደንብ ውጭ አቶ ዮናስ ያልወሰዱትን ብድር እንዲከፍሉ ያልተጠየቁ መሆኑን እንዲሁም የተፈፀመባቸው በደል አለመኖሩን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ዮናስ የብርጭቆ ወረቀት ፋብሪካን” ጨረታ አውጥቶ የሸጠው “በሴራ” ሳይሆን ፋብሪካው እዳውን መክፈል ባለመቻሉ “በኪሳራ” ነው ተብሏል።