ቀጥታ፡

ኢዜማ በመቀሌ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ተወያየ

መቀሌ መስከረም 4/2012 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ / ዛሬ በመቀሌ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አደረገ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱአለም አራጌ በውይይቱ ወቅት ፓርቲው በዜጎች የግል መብትና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ ፕሮግራም እንደሚከተል ገልጸዋል። "መንግስት በተመረጡ ውስን ጉዳዮች ካልሆነ በቀር በኢኮኖሚ ጉዳይ እጁ ማስገባት እንደሌበት ኢዜማ ያምናል "ብለዋል። ኢዜማ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር እንደሚቀበል ጠቅሰው ህገ መንግስቱ ጥሩ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ መሻሻል የሚገባቸው አንቀጾችም እንዳሉ ተናግረዋል። ፓርቲው ህገ መንግስቱ ግን መሻሻል አለበት ከማለት ውጭ መቀየር አለበት የሚል አቋም እንደሌለው ገልጸዋል። በኢዜማ አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች  የኢሳት ቴሌቭዥን በመጠቀም ጭምር የበደሉትን የትግራይን ህዝብ ይቅርታን ሳትጠይቁ ለምን መቀሌ መጣችሁ ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ይግኙበታል። የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው " በደል የፈጸመ  ተጸጽቶ ይቅርታ መጠየቅ አለበት እንጂ ይቅርታ እንዲጠይቅ መግፋት የለብንም "ብለዋል። በህዝብ ላይ ወንጀል የሚሰራ ማናቸውም የመገናኛ ብዙሃንና ግለሰብ በህግና በስርዓት መጠየቅ እንዳለበትም የተናገሩት ደግሞ ምክትል ሊቀመንበሩ ናቸው። "ሀገርን መገንባት የሚቻለው በውይይትና በሰከነ መንገድ ክርክር በማድርግ በመሆኑ በሰለጠነው መንገድ መጓዝ ይጠበቅብናል "ብለዋል። ኢዜማ በትግራይ መቀሌ ለህዝብ እራሱን  ለማስተዋወቅ  የክልሉ  መንግስት ላደረገው  ትብብር ምስጋና አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም