ቀጥታ፡

በንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ተቸግረናል-------የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

መስከረም 3/2012 የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ተቅማት አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ለችግሮች ተጋልጠናል ሲሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በትራንስፎርመር እጥረት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በከተማው አብሮ ጎዳና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፋንታው ተስፋወይ ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ የወንዝ ውሃን ለመጠጥነት እየተጠቀሙ ነው። ‘’ለመጠጥነት የምንጠቀመው የምንጭ ውሃ ንፅህናውን ያልጠበቀ በመሆኑ እኔም ሆንኩ ልጆቼ በተደጋጋሚ ለውሃ ወለድ በሽታዎች በመጋለጣችን በሌለን አቅም ለህክምና ወጭ ተዳርገናል‘’ ብለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን ለከተማ አስተዳደሩ ቢያቀርቡም በቅርብ ጊዜ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ ከማለት ውጭ ተግባራዊ ሲሆን ማየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ የከማዋ ነዋሪና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቤዛዊት ሸጋው እንዳለችው በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ ውሃ ለማግኘት በየእለቱ ረዢም ርቀት ጉዞ ታደርጋለች፡፡ ''በዚህም ባለፈው ዓመት በትምህርት ወቅት ውሃ ለመቅዳት ስል ሩቅ ቦታ ስለምጓዝ እንደሌሎች የክፍል ጓደኞቼ ትምህርቴን በአግባቡ እንዳልከታተል ተጽእኖ ፈጥሮብኝ ከርሟል" ብላለች። በአዲሱ የትምህርት ዘመንም ያለፈው ችግር እዳይደገም ስጋት እዳላት ገልጻ የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቃለች፡፡ ሌላኛው ነዋሪ አቶ አሰፋ ጣሰው በበኩላቸው ላለፉት ሶስት ዓመታት በማህበር ተደራጅተው ባገኙት ቦታ ላይ ቤት ሰርተው ቢኖሩም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ በችግር ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም የውሃ ተቋማት በመገንባታቸው ችግራችሁ ይፈታል ቢልም እስካሁን መፍትሄ አላገኘንም ሲሉ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ተናግዋል። የከተማው ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ የተነሱ ጥያቄዎች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ችግሩ የተፈጠረው በትራንፎርመር እጥረት መሆኑን ገልፀዋል። የህብረተሰቡን የንጹ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እያንዳንዳቸው በሰከንድ ስድስት ሊትር ውሃ ማመንጨት የሚችሉ አምስት አነስተኛ ምንጮች ተገንብተው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ የመነጨውን ውሃ ለከተማዋ ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ 150 ሺህ ሊትር መያዝ የሚችሉ ሁለት የውሃ ጋኖች ቢገነቡም በትራንስፎርመር ችግር ወደ ስራ ማስገባት ባለመቻሉ በመሃል ከተማ ያሉ ነዋሪዎች በፈረቃ ውሃ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ እንዳይከሰትም በ2010 ዓ.ም አራት ትራንስፎርመሮችን ለማስገባት ሁለት ሚሊየን ብር ለሰቆጣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢከፈልም እካሁን ማቅረብ ባለመቻሉ ከ17 ሺህ ላይ የከተማዋ ነዋሪ ህብረተሰብ ለችግር መጋለጡን አመልክዋል። የትራንስፈርመር ችግሩ እንዲቀረፍም ለሚመለከታቸው የወልደያ እና ለባህርዳር የአገልግሎት መስጫ ማእከላት በአካል እና በደብዳቤ ቢያሳውቁም እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ነው አቶ አብርሃም የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወልደያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አበራ በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ገንዘቡ ቢከፈላቸውም በአገር አቀፍ ደረጃ የትራንስፈርመር እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ማቅረብ አለመቻላቸው ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም