በየተሰማሩበት መስክ አቅደው ለውጥ ለማምጣት እንደሚተጉ በኦሮሚያ ሁለት ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ

45
መስከረም 2 /2012 በተያዘው አዲስ ዓመት በየተሰማሩበት መስክ አቅደው በመንቀሳቀስ ለለውጥ ተግተው እንደሚሰሩ በኦሮሚያ ኢሉአባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ለውጠው ለሀገር ልማት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው። ወጣት ፈቃዱ መኮንን በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ነው። ቀደም ሲል አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በመቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ዕቅድ ባለማውጣቱ በሚፈለገው ደረጃ ራሱን መቀየር ሳይችል መቅረቱን ተናግሯል። "ስራዎችን ስሰራም ይሁን ገንዘብ ሳወጣ በዘፈቀደ ነበር" ያለው ወጣቱ ይህም የሚያገኘውን ገቢ በአግባቡ እንዳይጠቀምበት እንዳደረገው አስታውሷል። በተጀመረው አዲስ ዓመት በግሉ የሚሰማራበትን የስራ መስክ ለይቶ በማቀድ ከቤተሰብ ጠባቂነት ተላቆ እራሱን በመቻል ለውጥ ለማምጠት ተግቶ እንደሚሰራ ተናግሯል። በከተማው በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት ሲሳይ አቤ በበኩላቸው የ2012 የስራ ዘመን ዕቅዳቸው ከቤተሰብ ጀምሮ በሀገር ሰላም ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። "የሀገር ሰላም የሚረጋገጠው እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላም መስፈን የሚጠበቅበትን ሲወጣ ብቻ ነው" ያሉት መምህሩ ከቤት ውስጥና ከአካባቢ ጀምሮ ሰላም የተከበረ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። “ ወደ አዲሱ ዓመት ስንሸጋገር ያለፈውን ዓመት መልካም ስራዎችና ጉድለቶችን በመገምገም መሆን አለበት” ብለዋል:: ወጣቶች በመልካም ስነምግባር እንዲያድጉ እና ለሀገር እድገት የሚጨነቁ እንዲሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ሚናቸውን መወጣት የአዲሱ ዓመት ዕቅዳቸው መሆኑን ገልጸዋል። በቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወጣት ኤሊያስ ጅፋር በሰጠው አስተያየት ከዚህ ቀደም በአብዛኛው ዓመት በመጣ ቁጥር ለመለወጥ ቢያስብም በፈለገው መልኩ ሊሳካለት እንዳልቻለ ተናግሯል። ለዚህም ምክንያቱ አቅዶ ለመፈጸም የተነሳሽነት ማጣት ፣ የጊዜና ገንዘብ አጠቃቀም ችግር እንደሆነ አመልክቷል። በተያዘው አዲስ ዓመት የነበረበትን ችግር ለመፍታት የስራ መከታተያ ማስታወሻ አደራጅቶ በዕቅድ ለመመራት እንደተዘጋጀ ገልጿል። ሌኛው አስተያየት ሰጪ በዞኑ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የገበያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ጅብሪል ሁሴን ናቸው:: እሳቸው እንዳሉት በተለይ ከስራቸው አንፃር ባለፈው ዓመትም እንደ ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየው ያለአግባብ በሆነ የዋጋ ጭማሪ የገበያ ዋጋ መናር ነው። እንደ ተቋም በአዲሱ ዓመት ይሄንን ችግር ለማቃለል ከተለያዩ ማህበራት ጋር በመሆን የገበያ ትስስር መፍጠርና ምቹ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መስራት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫቸው እንደሆነ አመልክተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በየተሰማሩበት መስክ አቅደው በመንቀሳቀስ እራሳቸውን በመለወጥ ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገራቸው ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም