ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በነሀሴ ወር 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 41 ሺህ 339 ቶን ምርቶችን አገበያየ

መሰከረም 2/2012 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው ነሐሴ ወር 2011 ዓም በጠቅላላው 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 41 ሺህ 339 ቶን ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ። በአማራጭነት ሲገበያዩ የቆዩት ቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ አስገዳጅ ሆነው ግብይታቸው በምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲካሄድ መወሰኑም ተጠቅሷል፡፡ የእነዚህን ምርቶች ኮንትራት በማሻሻልና የመረከቢያ ቅርንጫፎችን ዝግጁ በማድረግ ከሚመጣው ምርት ዘመን ጀምሮ በስፋት ለማገበያየት መዘጋጀቱን የምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ ምርቶቹ በምርት ገበያ እንዲገበያዩ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መወሰኑ የኮንትሮባንድ ንግድንና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ እንዲሁም የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ይረዳል፡፡ እንዲሁም ኑግ 10ኛ ምርት ሆኖ በቅርቡ ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ይቀላቀላል ሲል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አመልክቷል። ምርት ገበያ በነሐሴ ወር 2011 ዓም 25 ሺህ 386 ቶን ቡና፣ 5 ሺ115 ቶን ሰሊጥ፣ 1 ሺህ 386 ቶን ነጭ ቦሎቄ፣ 7 ሺ 498 ቶን አኩሪ አተርና 1 ሺ 955 ቶን አረንጓዴ ማሾ በአጠቃላይ 41 ሺህ 339 ቶን  ምርት  በ2 ነጥብ 42 ቢሊየን ብር አገበያይቷል፡፡ በወሩ በምርት ገበያው ከተገበያዩት ምርቶች ውስጥ ቡና 61 በመቶ የግብይት መጠንና 80 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በ22 የግብይት ቀናት ሁሉም የቡና ዓይነቶች ለግብይት ቀርበው በምርት ገበያው የግብይት መድረክ በ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተገበያይተዋል። ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና 70 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ፤  ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርብ ቡናና ስፔሻሊቲ ቡና ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግበዋል፡፡ የዚህ ወር የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 22 በመቶ የግብይት መጠንና 35 በመቶ የግብይት ዋጋ ጭማሪ ሲያስመዘግብ አማካይ ዋጋውም አስር በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህ ወር 5 ሺ 115 ቶን ሰሊጥ በ29 ነጥብ 79 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁመራ/ ጎንደር ሰሊጥ 70 እና 73 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ ትልቁን የግብይት ድርሻ አስመዝግቧል፡፡ አማካይ የሰሊጥ ዋጋም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በአምስት በመቶ ጨምሯል፡፡ በነሀሴ ወር 2011 ዓ.ም በአጠቃላይ 1 ሺ 386 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ28 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ21 በመቶ ቢቀንስም የግብይት ዋጋው ግን በ21 በመቶ አድጓል፡፡ እንዲሁም በወሩ 7 ሺ 498 ቶን አኩሪ አተር በ115 ነጥብ 32 ሚሊየን ብር ሲገበያይ ከዚህ ውስጥ የጎጃም አኩሪ አተር 70 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በተጠቀሰው ወር 1 ሺህ 955 ቶን አረንጓዴ ማሾ ለግብይት ቀርቦ በ58 ነጥብ 34 ሚሊየን ብር መገበያየቱን ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም