የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አንድነትን የሚንድ አፍራሽ አሉባልታ ሳይበግረው አገሩን እያገለገለ ነው - የሰራዊቱ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አንድነትን የሚንድ አፍራሽ አሉባልታ ሳይበግረው አገሩን እያገለገለ ነው - የሰራዊቱ አባላት
መስከረም 2/2012 የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አንድነትን የሚንድ አፍራሽ አሉባልታ ሳይበግረው ሀገርና ህዝብን በታማኝነት እያገለገለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሠራዊቱ አባላት ገለፁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰራዊቱን በተመለከተ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩት አሉባልታዎች የሠራዊቱን አንድነትና ሀገራዊ ወገንተኝነት ሊሸረሽሩት እንዳልቻሉ ነው የሠራዊቱ አባላት የተናገሩት። ይልቁንም ሠራዊቱ እነዚህ አፍራሽ አሉባልታዎች ሳይበግሩት የአገሪቷን ሕዝቦች ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላቀ መልኩ ጠንክሮ እየሰራ ነውም ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ ምን ጊዜም ለሕዝብ በመቆም ሕዝባዊነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልፀዋል። ይህንን ለአገርና ለሕዝብ ያለውን ፍቅር በተግባር እያሰመሰከረ የሚቀጥል መሆኑንም አመልክተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መጋቢ አምሳ አለቃ መልሰው ተውው እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህብራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሠራዊቱ ላይ በርካታ የሃሰት ወሬዎች ይሰራጫሉ። ሆኖም ሠራዊቱ ለአንዱ የሚወገንበት የተለየ ዓላማ እንደሌለው ስለሚታወቅ በከፍተኛ ትጋት አገርንና ሕዝብን እያገለገለ ነው ብለዋል። ''በተለይ ደግሞ ብሔርን መሰረት አድርገው የሚነዙ አስተሳሰቦች በሠራዊቱ ውስጥ ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም'' ያሉት መጋቢ አምሳ አለቃ፤ ብሔር የሚኖረው አገር ሲኖር ብቻ ነው ሲሉም አመልክተዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ምክትል አስር አለቃ ስመኝ ማሬም እንዲሁ በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሠራዊቱ ብዝሃነትን አክብሮ ለአገራዊ አንድነት እየሰራ ነው ብለዋል። ከውጪ ሆነው ጭምር መከላከያ ሠራዊቱን በተመለከተ በርካታ የሀሰት መሬዎችንና አሉባልታዎችን የሚያቀነባብሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው ይህ ግን በሠራዊቱ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅእኖ እንዳላስከተለ ገልፀዋል። ወደፊትም የሠራዊቱ አንድነት በተሻለ መልኩ ተጠብቆ የአገሪቷን ሉኣላዊ አንድነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ምክትል አስር አለቃ ስመኝ ተናግረዋል። "ሠራዊቱ ከሕዝብ የወጣ ለሕዝብ የቆመ በመሆኑ ሕዝባዊነቱ ይቀጥላል" ያሉት ደግሞ አስር አለቃ ሻሚል መሓመድ ናቸው። አስር አለቃ ሻሚል አክለውም ሠራዊቱ በየትኛውም መስፈርት ከብሔርና ከኃይማኖት ጋር ግንኙነት የሌለውና ነጻነቱን ጠብቆ ሕዝቡን በማስቀደም እያገለገለ ይገኛል ብለዋል። ወታደር ኢማን ዘላለምም በበኩላቸው ሠራዊቱ ከውጪ የሚነዛውን አፍራሽ እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ሊቀበለው አይችልም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ምክንያቱም ሠራዊቱ የተገነባው ሕዝብን በእኩልነትና ሚዛናዊነት ማገልገል በሚያስችለው መንገድ በመሆኑ ነው ሲሉም አክለዋል። ይሁን እንጂ ከውጪ ሆነው ሠራዊቱን ለመከፋፈል የሚንቀሳቀሱ አካላት አሁንም በመኖራቸው ሠራዊቱም ይህንን አፍራሽ ተልዕኮ ለመከላከል ራሱን ዝግጁ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።