በዓለም ዋንጫው በስፔንና ፖርቹጋል መካከል ዛሬ የሚደረገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ከሁለተኛ ቀን መርሃ ግብሮች መካከል በዓለም እግር ኳስ ኃያል አገሮች የሚባሉት  ስፔንና ፖርቹጋል በምድብ ሶስት የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን በሶቺ ከተማ 45 ሺህ 659 ተመልካች በሚያስተናገደው ፊስት ስታዲየም ከምሽቱ 3 ሰአት ላይ ያደርጋሉ።  ስፔን ዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ ሁለት ቀናት በፊት የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአገሪቷን አሰልጣኝ ዩለን ሌፕቴጉዊን ከስራቸው ማሰናበታቸው ያልተጠበቀ ውሳኔ ነበር። አሰልጣኙ የተሰናበቱበት ምክንያት ያለ ፌዴሬሽኑ እውቅና የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ለመሆን መስማማታቸው እንደሆነ ተገልጿል።  በሌፕቴጉዊ ምትክ የቀድሞ የስፔን ብሔራዊ ቡድን የመሐል ተከላከይ ፈርናንዶ ሂዬሮ የተሾሙ ሲሆን ዛሬ ከፖርቹጋል ጋር በሚደረገው ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑን ይመራሉ።  ፈርናንዶ ሂዬሮ ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት አሰልጣኝ ሆኜ ከተሾምኩበት ጊዜ እስከ ፖርቹጋሉ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ለማምጣት አቅም እንደሌለና በጥቂት ቀናቶች ሊለወጥ የሚችል ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። 'ቡድኔ በጥሩ መነሳሳት ላይ ይገኛል ትልቅ የሚባል እድል አለን ትኩረታችን ወደ ሩሲያ ስንመጣ ልናሳከው ያቀድነው ግብ ላይ መሆን አለበት የዓለም ዋንጫውን ለማንሳት እንፋለማለን' ብለዋል። የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮኖቹ ፓርቹጋል በአህጉራዊ ውድድር ላይ የሰሩትን ታሪክ በዓለም ዋንጫው ላይ ለመድገም ሩሲያ መክተማቸውን ተናግረዋል። የፖርቹጋል ተከላካይ መስመር ተጫውተው ባለፉት የ63 ዓመቱ ፈርናንዶ ሳንቶስ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በአውሮፓ ዋንጫ ስኬት ወደ ዓለም ዋንጫው ሲመጡ ትልቅ የራስ መተማመን ፈጥሮላቸዋል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስ ስፔን ዓለም ዋንጫው ጥቂት ቀናት ሲቀሩት አሰልጣኟን ማሰናበቷ በምንም አይነት መልኩ አያደክማትም ሲሉ ተናግረዋል።  ስፔንና ፖርቹጋል በዓለም ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ 16 ውስጥ ተገናኝተው ስፔን በዴቪድ ሲልቫ ጎል አንድ ለዜሮ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን ስፔን ዓለም ዋንጫውንም ማሸነፏ የሚታወስ ነው። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች እስካሁን 35 ጊዜ ተገናኝተው ስፔን 16 ጊዜ ስታሸንፍ ፖርቹጋል 6 ጊዜ አሸንፋለች የተቀረውን 13 ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።  ስፔን በቅጽል ስማቸው ላሮሀ (ቀዮቹ) እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን ፓርቹጋሎች ከአገራቸው ምስረታ የተያያዘ ሴሌሳኦ ዳስ ኩዊናስ የሚል ስያሜ አላቸው።  የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ የ44 ዓመቱ ጣልያናዊው ጂያንሉካ ሮቺ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።  ከፖርቹጋልና ስፔን ጨዋታ በተጨማሪ ዛሬ በዓለም ዋንጫው ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በምድብ አንድ ግብጽና ኡራጓይ በኢካቴሪንበርግ አሬና ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ግብጻዊው መሐመድ ሳላህ ከጉዳቱ አገግሞ በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።  በምድብ ሶስት በቅዱስ ፒተርስበርግ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ሞሮኮና ኢራን ይጫወታሉ። ትናንት በዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇ ሩሲያ በዴኒስ ቼሪሼቭ ሁለት ግቦች እንዲሁም በዩሪ ካዚኒስኪ፣ አርተም ዝዩባና አሌክሳንደር ጎሎቪን አንድ አንድ ግቦች ሳዑዲ አረቢያን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፏ ይታወሳል። ለሩሲያው ክለብ ክራስኖዳር የሚጫወተው የ28 ዓመቱ ዩሪ ካዚኒስኪ በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን አሌክሳንደር ጎሎቪን በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያውን ቢጫ ካርድ የተመዘዘበት ተጫዋች ሆኗል። የዓለም ዋንጫው እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም