የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሂውስተን አዲስ በረራ ሊጀምር ነው

260
መስከረም 1/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ ሂውስተን በሳምንት ሶስት ቀን በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ በታህሳስ 2012 ዓ.ም ወደ ሂውስተን በሳምንት ሶስት ጊዜ የበረራ አገልግሎት እንደሚጀምር የአየር መንገዱ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሂውስተን የሚያደርገው በረራ ከዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስና ቺካጎ በመቀጠል በአሜሪካ ያለውን መደረሻ ወደ አምስት ከፍ ያደርገዋል። ሂውስተን በቴክሳስ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በአሜሪካ ብዙ ህዝብ ከሚኖርባቸው ከተሞች በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ብዛት ያላቸውን የጤና አገልግሎት እና የምርምር ተቋማትን የያዘች ናት። የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) ወደ ህዋ የሚደረጉ ጉዞዎችን የሚቆጣጠር የጆንሰን የህዋ ማዕከልም በሂውስተን ከተማ ነው የሚገኘው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት ከ120 በላይ የበረራ መዳረሻዎች ሲኖሩት ከዚህ ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ መዳራሻዎች ናቸው። በአገር ውስጥም 21 መደረሻዎች አንዳሉት ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ ባንጋሎር ከተማ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በረራ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁም ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም