ቀጥታ፡

ዚምባቡዌያውን ለቀድሞው ፕሬዝዳንታቸው ሮበርት ሙጋቤ ከዛሬ ጀምሮ በሩፋሮ ስታዲየም ሃዘናቸውን ይገልፃሉ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 1/2012 ዚምባቡዌያውን ለቀድሞው የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከዛሬ ጀምሮ አስክሬኑ በሚቆይበት ሀራሬ በሚገኘው ሩፋሮ ስታዲየም ሃዘናቸውን ይገልፃሉ። የዚምባቡዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ በሲንጋፖር ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ጳጌሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በ95 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። አስክሬናቸው ትናንት ወደ አገራቸው ሲገባ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አስክሬኑ የሐራሬ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደረስ አቀባበል አድርገዋል። አስክሬናቸው ሀራሬ በሚገኘው ሩፋሮ ስታዲየም ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዚምባቡዌ ዜጎች በስታዲየሙ በመገኘት ሀዘናቸውን እንደሚገልፁ ቢቢሲ ዘግቧል። ዚምባቡዌያውን ከአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ወደ ሐራሬ በመምጣት የሮበርት ሙጋቤ አስክሬንን ይመለከታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። የሮበርት ሙጋቤ አስክሬን ለሁለት ቀናት በሩፋሮ ስታዲየም ከቆየ በኋላ ከነገ በስቲያ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ዝቪምባ የሚሄድ ሲሆን በዛው ዕለት የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድም ተጠቅሷል። የቀብር ስነ ስርዓቱ እሁድ መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚከናወንና እስካሁን ድረስ ቀብሩ የሚካሄድበት ስፍራ እንዳልተወሰነ ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል። የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እ.አ.አ በ1924 ነው የተወለዱት። አገሪቷ (በቀድሞ መጠሪያዋ ደቡብ ሮዴሺያ) እ.አ.አ በ1980 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ የመጀመሪያው የዚምባቡዌ መሪ ሙጋቤ ነበሩ። እ.አ.አ በ1980 የተካሄደውን የመጀመሪያ ምርጫ በማሸነፍ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ እ.አ.አ በ1987 የዚምባቡዌ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል። አገራቸውን ለ37 ዓመት ከመሩ በኋላ እ.አ.አ በ2017 የአገሪቷ መከላከያ ሃይል ከስልጣናቸው እንዲነሱ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ሮበርት ሙጋቤ ከሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ህይወታቸው እስከሚያልፍበት ቀን ድረስ በሲንጋፖር ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም