ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋና ባህላዊ ሀብቶቿን በአግባቡ ማስተዋወቅ አለባት----አፍሪካዊያንና ታዋቂ ግለሰቦች

አክሱም ኢዜአ መስከረም 1/ 2012 ዓ.ም---ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋና ለዓለም የሚተርፍ ባህላዊ ሀብቶቿን በአግባቡ ማስተዋወቅ እንዳለባት በዓሉን ምክንያት በማድረግ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አፍሪካዊያንና ታዋቂ ግለሰቦች ተናገሩ። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የቀን መቁጠሪያና የዘመን መለወጫ ያላት ሀገር በመሆኗ ልዩ እንደሚያደርጋትም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት። አዲስ ዓመትን ለማክበር ከዚምባቡዌ እንደመጣ የገለጸው ሚስተር ፓትሪክ ኩዋና በበዓሉ ከኢትዮጵያዊያን ወንደሞቹ ጋር በማሳለፉ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል። “ኢትዮጵያን ማየት ትልቅ እድል ነው፤ ብዙ የተፈጥሮና ታሪካዊ ሀብቶች ያላት ሀገር ናት” ያለው ሚስተር ፓትሪክ እዚህ ተገኝቶ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በዓሉን በማክበሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረለት ተናግሯል። ኢትዮጵያ ያላት ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች እንዲሁም የህዝቦች ብዝሀነት የተለየ እንደሚያደርጋትና የተፈጥሮ ሀብቷም ለአፍሪካውያን ጭምር እንደሚተርፍ ገልፅዋል። እነዚህ ሀብቶቿን ለአፍሪካና ለዓለም በሚገባ በማስተዋወቅ የቱሪዝም እንቅስቃሴዋን ልታሳድግ እንደሚገባም አመልክቷል። “በአዲስ ዓመት እዚህ በመምጣቴ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተለየ የቀን መቁጠሪያና የዘመን መለወጫ ያላት ሀገር መሆኗን አውቄያለሁ፣ ይሄ ለእኔ አዲስ ነው” ያለችው ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የመጣችው ሚስ ሲዶኒን ፈሪራ ናት። “ወደኢትዮጵያ ከመጣሁ አንስቶ አገሪቷ የጥንት ስልጣኔና የቅርስ ባለቤት እንዲሁም የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር መሆንዋን አውቄያለሁ፣ የታሪክም ባለቤት ናት ይህም ያኮራል” ያለችው ሚስ ሶዶኒን፣ ሀገሪቷ ላሏት ባህላዊ ሀብቶችና የተፈጥሮ ጸጋዎች ተገቢ ትኩረት ስጥታ ማስተዋወቅ እንዳለባት ተናግራለች። በተባበሩት አፍሪካ የንጉሳውያን ማህበር የአፍሪካ ሕብረት እና የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ብሩክ ተመስገን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ብዙ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ሃብት ብትይዝም በማስተዋወቅና ለአለም በማዳረስ በኩል ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል። “ያለንን የሚያኮራ እና ለዓለም የሚተረፍ ሃብት ተደጋግፈን ማስተዋወቅ እና ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርብናል ያሉት” አቶ ብሩክ የብዙ ታሪክ፣ ባህልና ብዝሃነት ባለቤት መሆንን በመልካም አጋጣሚነት በመውሰድ ለበጎ ተግባር ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል። ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በአንድ ሀገር አብረው መኖራቸው እንደሚያስደስት ገልጸው፣ “በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን በብሔር መከፋፈል እና ጥላቻን በማስወገድ አንድነትን አጠንክሮ ወደልማት እና ብልጽግና መምጣት ይኖርብናል” ብለዋል። አብሮነትና ፍቅርን ማጠናከርና አዕምሮን ለበጎ ተግባር ማዋል ከተቻለ አገሪቱን ማሳደግና ለሌሎች መትረፍ እንደሚቻል አቶ ብሩክ ገልጸው፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጸጋና ባህላዊ ሀብቶች በማስተዋወቅ በኩል ሁሉም የድርሻውን አውቆ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል። በበጎ አድራጊነታቸው የሚታወቁት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት ይግዛው በበኩላቸው “ዛሬ የተቀበልነው አዲሱ ዓመት ሀገርና አንድነትን የምናጠናክረበት ዘመን ሊሆን ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ፣ ፍቅር ወዳድ እና ተግባቢ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ መሰረት በአዲሱ አመት ህዝቡን እርስ በርስ ለማለያየትና ለማጥላላት የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ነው የገለጹት። “ኢትዮጵያ የፍቅርና የአንድነት ሀገር መሆኗን በመዘንጋት እርስ በርስ መለያየትና መነጣጠል አግባብ አይደለም” ብለዋል። በብሔር፣ በፖለቲካ እና በሃይማኖት በመለያየት ማንም አትራፊ እንደማይሆን ተገንዝቦ የቆየ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም