ኢትዮጵያዊያን እድገትንና ብልጽግናን መጎናፀፍ የሚችሉት አንድነታቸውን ማጥበቅ ሲችሉ ብቻ ነው - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን እድገትንና ብልጽግናን መጎናፀፍ የሚችሉት አንድነታቸውን ማጥበቅ ሲችሉ ብቻ ነው - የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 6/2011ኢትዮጵያዊያን ድህነትን በማስወገድ የእድገትና ብልጽግናን ፍሬ ማየት የሚችሉት የሚያለያዩዋቸውን ጉዳዮች በጋራ በመፍታት አንድነታቸውን ማጥበቅ ሲችሉ ብቻ መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ገለፁ። የብሄራዊ አንድነት ቀን ዛሬ በብሄራዊ ቤተ-መንግስት በታላቅ ስነ-ስርዓት ሲካሄድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክስቲያናት መሪዎች መልክታቸውን አስተላልፈዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት የሃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት ትውልዱ የአገሪቷን አንድነትና ሰላም ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል። 'መለያየት፣ ጥልና ጥላቻ ባለበት ቦታ ፈጣሪ አይገኝም፤ ይልቁንም የዚህ ዓይነት ተግባር በሚፈፀምበት ቦታ የፈጣሪ ፀጋ ይርቃል' ያሉት የሀይማኖት አባቶቹ፤ "የተለያየ በቀላሉ ይወድቃል፤ የተባበረ ግን ይፀናል" የሚለውን ሀሳብ ነው በአጽንኦት የገለጹት። በኢትዮጵያ የተዘራው የሚያፈራበት፣ የተተከለው ደግሞ የሚበቅልበት ምድር ትሆን ዘንድ መላው ዜጋ ጥላቻንና ጥርጣሬን በማስወገድ ለአንድነትና ለሰላም እንዲተጋ የሃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዘመን ሲቀበሉ በመካከላቸው ያለውን አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ለማጠናከር ቃል በመግባት መሆን አለበት። "ምክንያቱም ፈጣሪ የሰጠንን ይህን ምድር የምትለማ ወይም የምትጠፋ የምናደርጋት እኛው ፍጡራን ነን፤ መልካም ከሰራንም መልካም የምናተርፈው እኛው ነን፤ ክፉ ከሰራንም እንደዚያም ፍሬው ክፋት ነው" በማለት ፓትሪያርኩ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ከመንግስት ባለስልጣናት ጀምሮ እስከታች ያለው ኢትዮጵያዊ ራሱን የሚፈትሽበት፣ ያጠፋውንና የሰራውን የሚለካበትና ከስህተቱ ተፀፅቶ "መልካም ተግባር የሚተልምበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል። በተለይ የአገሪቷን አንድነት በተመለከተ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በእምነት ደረጃ ተመሳሳይ የሆነ አቋም አለ ያሉት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር፤ ይህንን የጋራ አቋም ከቃል ባለፈ ወደተግባር ለመተርጎም መላው ኢትዮጵያዊያን ቃል ሊገቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አንድነትን ለማጠናከር ከላይ ጀምሮ እስከታችኛው እርከን ያለው የመንግስት አስተዳዳር አገራዊና ህዝባዊ አመለካከቱ የተጠናከረ እንዲሆን አሳስበዋል። ህዝብና መንግስትን፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም በመካከሉ መግባባትንና መተሳሰብን ማጎልበትና አለበት ሲሉም ነው የሃይማኖት አባቶቹ የመከሩት። ይህም ነው ድህነትን በማስወገድ የእድገትና ብልጽግናን ፍሬ ለማየት የሚችለው ብለዋል። "አንድነት ውበት ነው" በማለት መልዕክታቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የውጭ አገር ሰዎች እንደቤታቸው የሚኖሩባት፣ ሌሎችን በታላቅ አክብሮትና ፍቅር የሚያስተናግዱ ህዝቦች የሚኖሩባት ምድር መሆኗን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ እንዳሉት፤ ደግሞ የብሄርን ጉዳይ ከሚገባው በላይ ማጦዝ ለኢትዮጵያ አይበጅም፤ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈፀም የሚደረግ ሙከራም ዘላቂነት ያለውን ሰላም ለማግኘት አያስችልም። ችግሮችንና ጥያቄዎችን በውይይትና በመግባባት መፍታት ነው ዘላቂ ሰላምን የሚያጎናፅፈው ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ መገፋፋት ተወግዶ አንድነትና ፍቅር ይሰፍን ዘንድ ተመኝተዋል።