ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት ለሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

አሶሳ (ኢዜአ) ጳጉሜን 6 ቀን 2011በአዲሱ ዓመት በክልላቸው ሰላምና ልማትን ለማምጣት በሚከናወኑ ተግባራት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የ2011 ዓመት በአሶሳ ከተማም ሆነ በክልሉ አሳዛኝ ግጭቶች ተስተናግደዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሃገር ሽማግሌው አቶ በፍቃዱ ወልደሰንበት ዘንድሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ብዙዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ለውጡ ወደሚፈለገው የእድገት ደረጃ እንዲያደርስ ሁሉም ሰው ሰላሙን አጠናክሮ መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል። "በተለይ ወጣቱ አጋጣሚውን በመልካምነት ሊጠቀም" ይገባል ያሉት የሃገር ሽማግሌው በቋንቋ እና ብሔር ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን ሊያጠናክሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች እንዲያተኩሩ መክረዋል። "እንደሃገር ሽማግሌ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012 መማር ማስተማር ሥራው ሠላማዊ እንዲሆንና የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ የድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል፡፡ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የሃገር ሠላም የሚረጋገጠው በጸጥታ አካላት ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል። "ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው ግጭት ብዙ ተምረናል" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው ያለው ሠላም ዘላቂነት እንዲኖረው ከሌሎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ መምህርቷ አመልክተዋል፡፡ ህብረተሰቡም ለራሱ ሰላም ዘብ በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ነው የገለጹት። በአሶሳ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ወጣት አንዋር መሃመድ በበኩሉ ሃገር ሠላም እንድትሆን ከጸሎት ባለፈ የወጣቶች ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጾ፣ በክረምት ወቅት ያከናወነው የበጎ አገልግሎት ተግባርን በበጋው ሰላምን በማስጠበቅ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ተናግሯል። በአሶሳ ከተማ በባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ የተሠማራው ወጣት ያሬድ ተስፋዬ በበኩሉ በአዲሱ ዓመት ያቀደውን ለማሳካት የከተማዋ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል። ዕቅዱ እንዲሳካ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማትና ጸጥታን የማረጋገጥ ስራዎች የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሠላምና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም