ቀጥታ፡

አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ሰላም፣ ብልጽግና እና አንድነት የሚጠናከርበት ሊሆን ይገባል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

ጳጉሜን 6 ቀን 2011 "በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብልጽግና እና አንድነት በማጠናከር ወደስኬት የምንረማመድበት እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ ይገባል" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዚዳንቷ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ለመላው ኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ መልዕክታቸው "አዲሱ ዓመት ተስፋን ሰንቀን ወደተሻለ ህይወት ለመሻገር የምንዘጋጅበትና ወደፊት ለመራመድ ራዕይ የምናስቀምጥበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል። በተጠናቀቀው ዓመት  አገሪቷ ብዙ ችግሮች እንዳሳለፈች ሁሉ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ገልጸው ፤ ሁሉም ዜጋ ተሳታፊ እንዲሆን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች መሰረት የጣሉ ስራዎች እንደተከናወኑበት ተናግረዋል። በተለይም የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በሩ መከፈቱንና በቀጣይም ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት መሰራት እንዳለበት ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል። በአመለካከታቸው የተነሳ ተራርቀው የቆዩ ዜጎች በአገር ጉዳይ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊወያዩ መብቃታቸውም ትልቅ ለውጥ መሆኑን አስረድተዋል። በአመለካከትና በእምነት መለያየት እንደ ምክንያት በመጥቀስ የጋራ ጉዳይን መሳት እንደማይገባም አስገንዝበዋል። "ከድህነት መላቀቅን፣ የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላትንና የመብቶቻችንን መከበር የጋራ ጉዳዮቻችን አድርገን በቅድሚያ መስራት አለብን" ብለዋል። ባለፉት ጊዜያት ያየናቸው አስከፊ ሁኔታዎች በአገሪቷ ዳግም እንዳይከሰቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ጎን በመቆም ለአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት ተባብረው መስራት እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል። አክለውም " በአዲሱ ዓመት አገሪቷን በጽኑ መሰረት ላይ የምናቆምበትና ተቋማዊ አሰራር በማጠናከር  አንድነትን የምናጎላበት ሊሆን ይገባል"  ብለዋል። ይህንንም ለማሳካት ከሕዝብ አቅም በላይ ባለመሆኑ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል። ለዚህም "አባቶቻችን ምስክር ናቸው" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ "በችግሮቻችን ተውጠን መቅረት ሳይሆን በእንቅፋቶች መካከልም የማይደበዝዙ ድንቅ ተግባራትን በማከናወን አገርን መገንባት ይቻላል" ብለዋል። በመጪው ዓመት ሰላሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ "ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ "ለዚህም አንድነታችን የማዕዘን ድንጋይ እንደሚሆን እምነቴ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያ የጤና፣ የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን  ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም