በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ስራ በአገሪቷ ያለው የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል - ብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ስራ በአገሪቷ ያለው የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል - ብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል
ጳጉሜ 6/2011 በኢትዮጵያ ከተጀመረው የለወጡ ሂደት ጋር ተያይዞ የነበረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግሮች እንዲፈታ መንግስት እያከናወነ ባለው ስራ በአገሪቱ ያለው የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን የብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል ገለፀ። የብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። ግብረ ኃይሉ ማምሻውን ለኢዜአ በላከው በዚሁ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት መግለጫ እንደገለፀው የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያ በተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት ላይ ሆና የሚከበር በመሆኑ ነው። ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና ከተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ለመውጣት መንግስት በአገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ መሆኑም ተጠቅሷል። በተከናወኑ ስራዎችም በአገሪቱ ያለው የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው ግብረ ኃይሉ ያመለከተው። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስት በጀመረው ጥረት ህብረተሰቡ ከግብረ ኃይሉ ጋር በመሆን በቅንጅትና በትብብር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት መቻሉ እንደ ትልቅ ስኬት ይወሰዳልም ብሏል። እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ግብረ ኃይሉ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር፤የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት እሴት እንዲጠናከር የማድረግ ተግባራትንም ያከናውናል ሲል አመልክቷል። እንዲሁም ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ያለ ምንም ፀጥታ ችግር እንዲካሄዱ የማድረግ ስራዎችን ግብረ ሃይሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሚሰራም አስታውቋል። ህብረተሰቡም በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውንም የፀጥታ ስጋት በመጠቆም እንደተለመደው ከግብረ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ያስተላለፈው መግለጫ መሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል:- ከብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብረ ኃይል የተሰጠ የአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች እንኳን ለ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት የሰላም፤ የጤናና የፍቅር መልካም ምኞት መግለጫዋች የሚቀርቡበት እንዲሁም የሀገራችን ሰላምና ደህንነት በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገኝ በጋራ የምንስራበት ዘመን እንደሚሆን እምነታችን ነው፡፡ የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል ልዩ የሚያደርገው ሀገራችን ኢትዮጵያ በተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት ላይ ሆና የምናከብረው መሆኑ ነው፡፡ የአዲስ ምዕራፍ መንደርደሪያ የሆነውን አዲሱን ዓመት ስናከብር ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋትና ከተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ለመውጣት መንግስት በአገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሠራ በመሆኑ የፀጥታና ደህንነት ሁኔታው እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጀመረው ጥረት ህብረተሰቡ ከፀጥታና ከፍትህ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን በቅንጀትና በትብብር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ መቻሉ እንደ ትልቅ ስኬት ይወሰዳል፡፡ለዚህም የብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ ግብር ኃይል ሰላም ወዳድ ለሆነው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናውን በታላቅ አክብሮት ያቀርባል፡፡ በቀጣይም እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ግብረ ኃይሉ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር፤የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት እሴት እንዲጠናከር የማድረግ እንዲሁም ሀይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ ባዓላት ያለ ምንም ፀጥታ ችግር እንዲካሄዱ የማድረግ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እንዲሚሰራ ማሳወቅ ይፈልጋል፡፡ በሀገሪቱና በህዝቦቿ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሽበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል ይሄንን እኩይ ተግባራ ሊፈፅሙ በሚችሉ የሽብር ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ የመውሰድና የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል የማድረግ ስራዎች በግብረ ኃይሉ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ለተከበረው ህዝባችን መግለፅ እንወዳለን፡፡ ግብረ ኃይሉ ማንኛውንም የአገርንና የህዝብን ህልውና ስጋት ላይ የሚጥሉ አደጋዎችን ለመቆጣጣር ከመቼውም ጊዜ በላይ ትክክለኛ ቁመና ላይ መሆኑን እያረጋገጠ፤ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከህብረተሰቡ ጋር እየተከናወኑ የሚገኙት የተቀናጁ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ግብረ ኃይሉ ሙሉ እምነት አለው፡፡ ህብረተሰቡ እስካሁን ድረስ ከፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጋር በቅንጀትና በትብብር እያደረገ ላለው እንቅስቃሴም ግብረ-ኃይሉ በድጋሚ ምስጋናውን እያቀረበ፤ በቀጣይ በሀገራችን ላይ የሚኖር ማንኛውንም የፀጥታ ስጋት በመጠቆም እንደተለመደው ከግብረ ኃይሉ ጎን በባለቤትነት እንዲቆም ጥሪ ያቀርባል፡፡ በድጋሚ አዲሱ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም የብልጽግና የአንድነት እንዲሆን ብሔራዊ የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል ይመኛል! መልካም አዲስ ዓመት!