ለዕቅድ መሳካት ቁርጠኛ መሆን ወሳኝ ነው - ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ለዕቅድ መሳካት ቁርጠኛ መሆን ወሳኝ ነው - ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ
ጳጉሜ 6/2011 አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የሚያቅዱ ሰዎች ዕቅዳቸውን ለማሳካት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ገለጸ። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የሚታቀዱ እቅዶች ከግብ እንዲደርሱ የጊዜ አጠቃቀም ባህልን ማሳደግ እንደሚገባም ተጠቁሟል። በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን በመካከለኛ በረጅም ርቀት ሩጫ የኢትዮጵያ ስም ከፍ ባለ የክብር ስፍራ እንዲቀመጥ ካስቻሉት ስመ ጥር አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት የሚወሳው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ''ሰው ለሚያቅደው ዕቅድ ቁርጠኛ መሆን አለበት'' ብሏል። በተሰማራበት መስክ ሁሉ ስኬታማ የሆነው ሻለቃ ሃይሌ ''ላቀደው ዕቅድ ቁርጠኛ የሆነ ሁሉ አቅሙን አውቆ ያቀደውን ዕቅድ ለመፈጸም እችላለሁ ብሎ ይነሳል'' ሲል አብራርቷል። ማንኛውም ዕቅድ ዓላማ ያለውና ስራው የሚፈልገው መርህ ሊኖረው እንደሚገባ ገልጿል። የህክምና ባለሙያው ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሰዓት አጠቃቀም ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት በስፋት መሰራት እዳለበት ጠቁመው፤ ለአገር እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለዜጎች ተጠቃሚነት ጊዜ የመጠቀም ልማድ ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አመልክተዋል።