ቀጥታ፡

በግ በስፋት ወደ ገበያ ቢገባም ዋጋው አልቀነሰም -- ሸማቾችና ነጋዴዎች

ጳጉሜ 6/2011 በአዲስ አበባ ከተማ  በዓሉን ምክንያት በማድረግ በግ በስፋት በገበያ ቢገኝም ዋጋው አለመቀነሱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡ በዊንጌት ጀሞና ብርጭቆ የበግ ንግድ ስፍራዎች ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች እንደጠቆሙት በርካታ በግ  ወደ ገበያው ቢገባም ዋጋው ግን ከባለፉት በኣላት ብዙም ቅናሽ አለመታየቱን ተናግረዋል፡፡ በጉለሌ ሸጎሌ አከባቢ ነዋሪ እንደሆነ የሚናገረው አቶ አበበ ካሳዬ የበግ ገበያው በየቦታው በስፋት እንደሚታይና ከባለፉት በዓላት የበዛ በግ በየቦታው ቢኖርም ዋጋው ግን በጣም እየናረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡ በአዲሱ ገበያም ሆነ በዊንጌት ደህና በግ ለመግዛት ፈልጎ እስከ አምስት ሺህ ብር መጠየቁን ተናግሯል፡፡ ከዚህ በፊት በጸጥታ ችግር ሳቢያ መንገድ ባለመኖሩ በግ በስፋት ወደገበያ ሳይገባ መቅረቱን ያወሳው አቶ አበበ አሁን ሰላም ሆኖ ዋጋው ያለመውረዱ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል ብሏል፡፡ በጀሞ አደባባይ በግ ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰብለ ታምራት አሁን በሶስት ሺህ አምስት መቶ የገዙት በግ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዋጋውም መጠኑም ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ተነጋግረው የገቡ ይመስላል ያሉት ወይዘሮ ሰብለ በግ ግን በየቦታው በስፋት መኖሩን ነው የጠቀሱት፡፡ ከጊንጪ ሁለት መቶ ያህል በግ ይዞ እንደመጣ የሚናገረው ዳንኤል ጸጋዬ በበኩሉ የበግ ገበያው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር በርካታ በግ ዘንድሮ መግባቱን ጠቁሞ ዋጋው ግን ከቦታው ሊቀንስ ባለመቻሉ እዚህም ሊወደድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ አምና ሀምሳ ያህል በጎችን ብቻ ይዞ መጥቶ መሸጡን የሚናገረው ዳንኤል ዘንድሮ በግ በብዛት በመግባቱ ገበያ ማግኘት ከባድ መሆኑን ይናገራል፡፡ ዘንድሮ የበግ ዋጋ ሊጨምር የቻለው የትራንስፖርት የመኖና ማደሪያ ዋጋ በመወደዱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከወሎንኮሚ ኢንጪኚ አንድ መቶ በግ ይዞ መምጣቱን የተናገረው ታጁ ፈይሳ ዘንድሮ ብዙ በጎች ወደ ገበያ በመምጣታቸው ገበያው ላይ ፉክክር መኖሩን ተናግሯል፡፡ በግ በብዛት በመኖሩ በግ አሳዳሪዎች በአንድ በግ እስከ ሁለት መቶ ብር እየጠየቁ መሆኑንና ትራንስፖርት ወጪውን እንዲሁ በመጨመሩ ሳቢያ የበግ  ዋጋው ላይ ጭማሪ እንዲኖር አድርጎታል ብሏል፡፡ በብርጭቆ በግ ገበያ ያገኘነውና ከአምቦ 500 በግ ይዞ እንደመጣ የሚናገረው አቶ ጣቡ ፈርሳ ባለፈው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ችግሮች ሳቢያ በግ ወደገበያ ለማምጣት እንዳልቻለ ተናግሮ ዘንድሮ ግን ሰላም ስለሆነ በርካታ ገበሬዎች በግ ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም