ቀጥታ፡

ፖሊስ በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

ጳጉሜ 6/2011 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ። አዲሱ 2012 ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ያለምንም ችግር በሰላም እንዲከበር የወንጀልና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሰራዊቱ አባላት በሙሉ በከተማዋ መሰማራታቸው ተገልጿል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዳሉት፤ በበዓላት ወቅት የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ስለሚጨምር በገበያና በመዝናኛ ስፍራዎች የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እንዲሁም ወንጀል እንዳይፈጸም ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። ህብረተሰቡ ባለፉት ጊዜያት በተከበሩ ሐይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት ያሳየውን ትብብር ዘንድሮም የፀጥታ ጉዳይ የጋራ መሆኑን በመገንዘብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ቀና ትብብር ኮሚሽነር ጌቱ ምስጋና አቅርበዋል። ኮሚሽነሩ በዓሉ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የደስታና የስኬት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት በነፃ የስልክ መስመር፤ በ991 እና 816 ወይም በ011 1 11 01 11 በመደወል ለኮሚሽኑ ማሳወቅ ይችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም