በአዲሱ ዓመት በይቅርታና በፍቅር አንድነታቸን የሚጠናከርበት መሆን አለበት - የእርቀ ሰላም ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት በይቅርታና በፍቅር አንድነታቸን የሚጠናከርበት መሆን አለበት - የእርቀ ሰላም ኮሚሽን
ጳጉሜ 6/2011 በጪው አዲስ ዓመት ዜጎች ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች የደረሰውን ጥፋት በመርሳት በፍቅር አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሆን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ። ሁሉም ሰው "እርቅ ያስፈልገናል" ከሚል መግባባት ላይ እንዲደርስ ማድረግ የኮሚሽኑ ቀጣይ ዓመት ዋነኛ ስራ እንደሚሆንም ተገልጿል። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን 2012 አዲስ ዓመት /ዘመን መለወጫ/ በዓልን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል። የኮሚሽኑ ሰብሰባቢ ብፁእ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ እንዳሉት፤ኢትዮጵያውያን የዳበረ የእርቀ ሰላም ባህል ባለቤቶች ናቸው። የሰላም ግንባታና እርቅ ደግሞ የሀገር ልማት መሰረቶች በመሆናቸው መጪው አዲስ ዓመት የፍቅር፣ የይቅርታና የመተሳሰብ እንዲሆን ተመኝተዋል። አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊነት ኩራት የሚሆንበት፣ ለሀገሩ የሚቆም ትውልድ የሚነሳበት፣ ህፃናት ቦርቀው የሚያድጉበት እናቶችና አባቶች የሚከበሩበት እንዲሆን ለሁም የበኩልን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል። "ባህላችን፣ ትውፊታችን፣ ወጋችን፣ ስርዓታችን ሳይጠፋ ይበልጥ የሚዳብርበት ዘመን እንዲሆንልን ከፈጣሪ እንጥይቅ" ብለዋል። ፈጣሪ የቸረንን በጎ ምግባር ጠብቀን፣ ከመራራቅ መቀራረብን፣ በልዩነት ከመራራቅ ተቀራርቦ መነጋገርን፣ ቂም በቀል ሳይሆን ይቅር ባይነትን የምናዳብርበት ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል። የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ፤ በመጪው አዲስ ዓመት ሁሉም ሰው "እርቅ ያስፈልገናል" ከሚል መግባባት ላይ ለማድረስ እንሰራለን ብለዋል። ህብረተሰቡ "እርቅ ያስፈልፈናል" ከሚል የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስ አበክሮ ማስተማር ይጠበቃልም ነው ያሉት። የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ እርቅ እንዴት ይተግበር የሚለውን ኢትዮጵያ ካላት የዳበር ባህላዊ እርቅ ጋር ተጣጥሞ ይሰራል ብለዋል። በመጨረሻም መጪው አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የብልፅግና እንዲሆን በመመኘት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።