ቀጥታ፡

አኩዋ ፓወር ኩባንያ በሶማሌና አፋር ክልሎች በ300 ሚሊዮን ዶላር የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ጨረታ ፕሮጀክት አሸነፈ

ጳጉሜ 6/2011 አኩዋ ፓወር የተባለ የሳዑዲአረቢያ ኩባንያ በሶማሌና አፋር ክልሎች በ300 ሚሊዮን ዶላር የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ጨረታ ፕሮጀክት አሸንፏል። የመንግስትና የግል አጋርነት ቦርድ የመጀመሪያውን ፕሮጀክት አጸደቀ። ገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ የመንግስትና የግል አጋርነት ቦርድ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔውን አሳልፏል። የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን 250 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል። በሶማሌ ክልል ጋድ እና በአፋር ክልል ዲቼቶ በተባሉት አካባቢዎች የሚገነባ ሲሆን የመጀመሪያው በመንግስትና የግል አጋርነት የሚሰራ የኃይል ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል። የኃይል ማመንጫው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ኤክትሪክ ኃይል የሚተላለፍ ሲሆን አንድ ኪሎ ዋት በ2 ነጥብ 526 ሳንቲም ዶላር መሆኑን ገልጸዋል። የመንግስትና የግል አጋርነት በመሰረተ ልማት፣ በኃይል ማመንጫ፣ በመንገዶች ፕሮጀክቶች ላይ በቀጣይ ተመሳሳይ ስራዎች እንደሚያከናውን ጠቁመዋል። አምስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጨረታ በቀጣይ እንደሚወጣም ዶክተር ተሾመ ገልጸዋል። አለም አቀፍ ጨረታ ከወጣ በኋላ የተለያዩ ማጣራት የተካሄደ ሲሆን ያሸነፈው ድርጅት በተለያዩ 11 አገሮች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን የሰራና ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም