ሠራዊቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል----ሜጀር ጄነራል ድሪባ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል----ሜጀር ጄነራል ድሪባ መኮንን
ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም ---የሀገር መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ድሪባ መኮንን ተናገሩ። ሜጀር ጄነራል ድሪባ ይህን ያሉት በሰላም ማስከበር ማዕከል ሁርሶ የተጠባባቂ ኃይል ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለዘጠነኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላት ባስመረቀበት ወቅት ነው፡፡ ሜጀር ጀነራል ድሪባ አክለው እንደገለፁት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አቅምና ብቃት ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ተደርጎ መገንባቱ ሰላም በማስከበር ተግባር ተመራጭ አድርጎታል፡፡ በተለይ ሠራዊቱ ለሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ አኩሪ ሥራ በመፈፀሙ በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ህብረት ተቀባይነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ነው የገለፁት፡፡ ‹‹ ሠራዊቱ ግዳጅ በሚፈጽምባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚፈጥረው ቅርበትና ማህበራዊ ተሳትፎዎቹ ተቀባይነቱን አሳድጎታል›› ሲሉም ሜጀር ጄነራል ድሪባ ገልጸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ሰራዊቱ በታላቅ የሙያ ፍቅርና ቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው ወታደራዊ ተግባራት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ እያገዘ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን የማስወገድ ስራው በቀጣናው ሁለንተናዊ ዕድገትና ትስስር ላይ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ሜጀር ጄነራል ድሪባ አመልክተዋል፡፡ የዘጠነኛው ዙር ተመራቂዎች ይህንኑ ኃላፊነት በታላቅ ቁርጠኝነት ለመፈፀም ወደ ደቡብ ሱዳንና አብዬ እንደሚጓዙም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሜጀር ጀነራል ድሪባ ገለጻ የሰራዊቱ አባላት ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ወታደራዊ ስነምግባር ሊፈጽሙ ይገባል። የሁርሶ የተጠባባቂ ሠራዊት ትምህርት ቤት (ኮንቲንጀንት) አዛዥ ኮሎኔል ሚልኬሳ ረጋሳ በበኩላቸው ሰልጣኞች ተግባር ተኮር አለም አቀፍ ዕውቀት መቅሰማቸውን ገልጸዋል። "ይህም የትኛውንም ግዳጅ በታላቅ ብቃት ለመወጣትና የሚያጋጥማቸውንም ማንኛወም መሰናክል በቀላሉ ለማለፍ ያስችላቸዋል" ብለዋል፡፡ የሰራዊቱ አባላት ለዓመታት ያካበቱት ልምድ ለተልዕኮው መሳካት ወሳኝ በመሆኑ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ተመራቂዎቹ በበኩላቸው ሀገራዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በወታደራዊ ስነምግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ ዜና የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ሞተራይዝድ ሻለቃ በአካባቢው ለሚኖሩ 40 ችግረኛ ህፃናት ተማሪዎች የደንብ ልብስ /ዩኒፎርም/ መግዣ12ሺህ ብር መለገሳቸው ታውቋል፡፡