መልካም አዲስ ዓመት -የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
መልካም አዲስ ዓመት -የኃይማኖት አባቶች
ጳግሜ 6/2011 አዲሱ ዓመት 2012 ዓ.ም በሀገራችን በሁለንተናዊ መልኩ ስኬትን የምናስመዘግብበት እንዲሆን የኃይማኖት አባቶቹ ልባዊ ምኞታቸውን ገለጹ። ፈጣሪ ቃል ኪዳኑን ጠብቆ ምድራችንን በልምላሜ፣ በአበባ፣ በፍሬ፣ በምርት በሁሉም ነገር አዲስ አድርጎታል ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ እኛ ሰዎችም በተመሳሳይ በአስተሳሰብ፣ በሥራና በአኗኗር ሁሉ ከልብ የሆነ መታደስ ሊኖረን ይገባልብለዋል። ብፁእነታቸው "የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናበስራለን'' የሚለው መልካም ምኞታችን ከቃላት አልፎ ተግባራዊ እንዲሆን ከሁሉም በፊት ይቅርታና እውነተኛ መግባባት በሁሉም ወገኖች መከናወን መቻል አለበት ሲሉም ተናግረዋል። አንድ መቀበል ያለብን እውነት በሐሳብ መቀራረብና በሰጥቶ መቀበል መርሕ እየተቻቻሉ መሄድ እንደ አዋጭ ባህል አድርገን መያዝ ካልቻልን "መቼም ቢሆን ለችግራችን መፍትሔ አናገኝም" ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ይህም በታሪክ የሁሉም ሃሳብ አንድ ዓይነት ሆኖ የተገኘበት ጊዜ የለምና ነው ብለዋል። ያለን ብቸኛ አማራጭ የተወሰነውን በመተው፣ የተወሰነውን በመቀበል፣ የተወሰነውን ደግሞ በመስጠት ወደ አንድነት መምጣትና ሀገርንና ወገንን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል። "ይህ ዓይነቱ መቻቻል በሀገራችን ውስጥ ባለመዳበሩ ሕዝባችንን ለመከራ ዳርጓል" ያሉት ፓትርያርኩ፤ ይህ ዓይነቱ ክስተት ከአሮጌው ጋር ማክተም አለበት ሲሉም አሳስበዋል። መለያየት፣ መገዳደል፣ ወገንን ማፈናቀል፣ አብያተ ሃይማኖትን መድፈር፣ የእርጅና ምልክቶች ናቸውና ከአሮጌው ዓመት ጋር አብረው ማለፋቸውን በአዲሱ ዓመት እናብስር ሲሉም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት አባቶች ፈጣሪቸውን በመፍራት ጥቅም ተኮር ሳይሆኑ ምዕመኑ የሚፈልገዉን አገልግሎት ብቻ መስጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። አዲስ ዓመት ማለት የሚያመልኩበት ቀን ብቻ ሳይሆን የሰሩትን መልካምና መጥፎ ስራዎችን የሚገመግሙበት እንዲሁም ወደ ፊት የሚሰሩትን ስራ የሚያቅዱበት እንደሆነም አብራርተዋል። "ፈጣሪዉን ፈርቶ የሚያገልግል የሃይማኖት መሪ ብዙ ተከታይ ያፈራል" ያሉት ሙፍቲ ሃጂ እንድሪስ፤ እሱ የሚናገረው ሃሳብ ተቀባይነት ያገኛል፣ እንዲሁም አገርንም ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት የማምጣት አቅም ይኖረዋልም ብለዋል። ሃጂ ሙፍቲ ኡመር አክለውም የሃይማኖት አባቶች፤ ወላጆችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መልካም ስራ በመስራት ለህፃናትና ወጣቶች አርአያ መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። መንግስት ወጣቶችን በአዲሱ ዓመት በመልካም ስራ ላይ በማሰማራት አገራቸውን እንዲያለሙና አገር ወዳድ እንዲሆኑ የአገራቸውን ሰላም ማምጣት እንዲችሉ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል ። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ሁሉም በየእምነቱ ፈጣሪውን በመፍራት ከመጥፎ ስራ በመቆጠብ በአንዲት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተከባብረው በመስራት ኑሮአቸውን ማሻሻል እንዳለባቸውም ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር መክረዋል። በመግለጫው ላይም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በምክር ቤቱ ተገኝተው ለሃጂ ሙፍቲ ኡመር የእንኳን አደረሰዎት ስጦታ አበርክተውላቸዋል። በዚሁ ጊዜ አዲሱ ዓመት በሀገሪቷ እውነተኛ ዕርቅ በማድረግ ፍጹም ሠላም የሚሰፍንበት፣ መደማመጥና መከባበር ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግ ሀገርንና ወገንን ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ የሚቻልበት ይሁን ያሉት ደግሞ የጉባዔው የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ መስዑድ አደም ሽፋ ናቸው ፡፡ በተመሳሳይ አዲሱ ዓመት መልካም ነገርን ለማቀድና ለመስራት ልባችንን ከፍተን በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት መንፈስ ይጀምር ዘንድ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን መልካም ምኞቷን አስተላለፈች። የሁሉም ዕቅዶቻችን ፍጻሜ የሚያገኙት ሠላም ሲኖር በመሆኑም ሁሉም ወጣት ለሰላም ዘብ እንዲቆም የቤተ ክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ መልዕክት አስተላልፈዋል። ለዚህም ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በ(ዮሐ.14፡17) “ሰላሜን እተውላችኋለሁ፤ ሠላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይነት አይደለም” ያለንን አስተውለን እንመርምር ብለዋል። ለመጪው ትውልድ የተመቻቸች ሀገር ለማስረከብ ባለፉት አመታት ያዘንንባቸውንና ለጋራ ዕድገት እንቅፋቶችን በማስተካከል በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ሁሉም ከጥፋት መንገድ እንዲወጣም ጠይቀዋል። ብፁዑ እንዳሉት፤ ጌታችን (በማቴ. 5፡12) “…እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን…” ብሎ ባስተማረን መሠረት በአዲሱ ዓመት ሁሉም ለአብሮነት፣ ለዕርቅና ለሠላም ይዘጋጅም ብለዋል። ሁሉም ምዕመን ከዕኩይ ተግባር ፈጻሚዎች ጋር ከመተባበር በመቆጠብና የታላላቅ አባቶችን ምክርን በመሰነቅ ሀገሩን ከጥፋት እንዲታደግም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔም ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላምና በጤና አሸጋገራችሁ እያለ አዲሱ ዓመት 2012 ዓ.ም በሀገራችን በሁለንተናዊ መልኩ ስኬትን የምናስመዘግብበት እንዲሆን ልባዊ ምኞቱን ገልጿል። የኃይማኖት አባቶቹ ለአገር ውስጥና ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በህመም ላይ ለሚገኙ፣ ለህግ ታራሚዎች፣ የአገሪቱን ዳር ድንበር በመጠበቅ ላይ ለተሰማሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን የመልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።