የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ
ጳግሜ 6/2011 የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ፡፡ የጣቢያው የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን አስተባባሪ አቶ ታፈሰ መንግስቱ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፈው ሳምንት የተያዙት እቃዎቹ ከጎረቤት አገር የገቡና በሁለት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች በድብቅ ሲጓጓዙ የተገኙ ናቸው። ከኮንትሮባንድ እቃዎቹ 3ሺ 440 የዓሳ ማስገሪያ መረቦች፤ 16ሺ 709 የሴቶች ሻርፕና 2ሺ 570 የልጆች ጅንስ ሱሪ ናቸው። የዓሳ ማስገሪያ መረቡ ለምግብነት ያልደረሱ የዓሳ ጫጩቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ መንግስት ቀደም ሲል ጥብቅ ክልከላ የጣለበት መሆኑንን አመልክተዋል። የኮንትሮባንድ እቃዎችን ያጓጓዙት ተሸከርካሪዎች አሸሬና ሳንጃ የተባሉትን የፍተሻ ኬላዎችን ጥሰው በማለፍ በላይ አርማጭሆ ወረዳ የጸጥታ ኃይል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ እንደአስተባባሪው ገለጻ ከአሽከርካሪዎቹ መካከል አንደኛው ቢሰወርም ሌላኛው ግን በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ነው። ህብረተሰቡ ለጣቢያው ሰራተኞች ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገው ጥረት የኮንትሮባንድ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል በቀጣይም ህብረተሰቡ ህገወጦችን በማጋለጥ የተጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያው አመልክቷል