የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ጳጉሜን 5/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሁለቱ አገራት የሁለትዮሸ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ከትናንት በስቲያ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ሩሲያ ማቅናታቸው የሚታወስ ነው። ሚኒስትሩ ዛሬ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ሞስኮ በሚገኘው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሩሲያ በጠላት ወረራ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን ከተሠለፉ ወዳጆች አንዷ መሆኗንም ጠቅሰዋል። በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መስክም ታዋቂው ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ትውልደ ኢትዮጵያዊና ሩሲያዊ መሆኑ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትጵያውያን በሩሲያ ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መደረጉ ሌላው የግንኙነቱ ጠንካራነት መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህንን በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባን ወዳጅነት በቴክኖሎጂ፣ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪና በባህል መስኮች ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ አገሮች በመጪው ጥቅምት 2012 ዓ.ም በሚያካሄዱት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትኩረት እንዲሠጥባቸው ለቀረቡት የትብብር መስኮች የቅርብ ክትትል በማድረግ ለውጤታማ ትብብር እንደሚሠራም አረጋግጠዋል። የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ ንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲሳተፉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ሩሲያ በኢትዮጵያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት መንደርደሪያና ኢትዮጵያም የአፍሪካ ደጃፍ መሆኗን በመጥቀስ፤ ሩሲያ በዕድሉ ልትጠቀም እንደሚገባ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣትና የኢኮኖሚ ትስስር የሚጎለብትበትን አማራጮች የማጠናከር ሥራ እየሠራች መሆኑን፤ በቅርቡም በሱዳን የተጫወተችው ዲፕሎማሲያዊ ሚና ለዚሁ ማረጋገጫና ዓይነተኛ ማሣያ መሆኑንም አመልክተዋል። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሩሲያ ቁልፍ አጋር ሃገር እንደሆነች በመግለጽ፤ በሁለቱ ሃገሮች መካከል በየጊዜው የሚደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ትብብሩን ወደ ላቀ ከፍታ እንደሚወስደው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት መስክ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምታራምደው ኃላፊነት የተሞላው የውጭ ግንኙነት ንም እንደሚያደንቁና ከሩሲያ ጋርም በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በጋራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል። የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በሽያጭ መስክ ብቻ ሳይሆን በተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መስክ ያላቸውን ሠፊ ልምድ ይዘው መግባት እንደሚፈልጉም አመልከተዋል። የሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢትዮጵያ ጋር በባዮሎጂ መስክ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎትም አስታውቀዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አኳያም በሩሲያ የዲፕሎማቲክ አካዳሚ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሚሠለጥኑበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹም ሰርጌ ላቭሮቭ ቃል ገብተዋል። የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለይ በማዕድን ፍለጋና ልማት ለሁለቱም ሃገራት የጋራ ጥቅም መሥራት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የፕሬስ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት የተሞላበት የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን አንስተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ይህን መሰል ውይይት መደረጉ ለግንኙነቱ መጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉዱ አንዳርጋቻው ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የልማት ትብብር ለማጠናከር አላማ ያደረገ ነውም ብለዋል። የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር 2018 በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል። በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል የተጀመረው ታሪካዊ ግንኙነት በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የሁለቱ አገሮች የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት በነበራቸው ግንኙነት አማካይነት ሲሆን የቤተክርስቲያናቱ ትብብር ለአገሮቹ ግንኙነት መሰረት እንደጣለም የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ። አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ1898 ሲሆን ባለፈው ዓመት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው 120ኛ ዓመት መከበሩም ይታወሳል።