በአዲሱ አመት ዳያስፖራውን በፋይናንስና ባንክ ዘርፍ እና በአነስተኛ መጠን የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ለማሳተፍ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ አመት ዳያስፖራውን በፋይናንስና ባንክ ዘርፍ እና በአነስተኛ መጠን የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ለማሳተፍ ታቅዷል
ጷጉሜ 5/2011 በአዲሱ አመት ዳያስፖራውን በፋይናንስና ባንክ ዘርፍ እና በአነስተኛ መጠን የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት እድሎች ለማሳተፍ መታቀዱን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። በአዲሱ አመት የዳያስፖራ ማህበረሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል። የብዙ ውጥኖች መጀመሪያ፣ መስኮች አረንጓዴ የሚለብሱበትና በአደይ አበቦች የሚያጌጡበት ዘመድ ወዳጅ የሚጠያየቅበት የዘመን መለወጫ በዓል ለኢትዮጵያውያን በርካታ ትርጉሞች አሉት። አዲስ አመት ሲመጣ መጪውን ዘመን ያማረ ለማድረግና ህይወትን ስኬታማ ለማድረግ ይታቀዳል፤ ለተግባራዊነቱም ይሰራል። ተስፋም ይሰነቃል። በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ፣ የእሬቻ፣ የደመራና ሌሎች በዓላትን በአገራቸው ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዳያስፖራውን በአገራዊ ጉዳዮች በስፋት ለማሳተፍ የሚያስችሉ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተዋል። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስና ባንክ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩና በአረብ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ታሳቢ ያደረጉ በአነስተኛ መጠን የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለመፍጠር ኤጀንሲው ማቀዱን ጠቁመዋል። ሀብት ማሰባሰብና ሌሎች ስራዎችን ለመሰራት መታቀዱንም ገልጸዋል። የዳያስፖራ ማህበረሰቡም በተዘጋጁት መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪ አቅርበዋል። ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት፤ በ2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዳያስፖራዎች በንግድና ኢንቨስትመንት የተሰማሩበት፣ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ያካፈሉበት፣ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉበትና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ስራዎች ያከናወኑበት ስኬታ አመት ነበር። በመጪው አዲስ አመትም ተመሳሳይ ተግባራትና ሌሎች ተጨማሪ ስራዎች ለማከናወን የተለያዩ የዳያስፖራ ማህበራትና ተቋማት ለመስራት ዕቅድ አውጥተው ማሳወቃቸውን አብራርተዋል። የዘመን መለወጫ በዓልና ሌሎች በዓላትን ለማክበር ወደ አገራቸው የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ታሳቢ በማድረግ ሆቴሎችና ሌሎች አገልገሎት ሰጪ ተቋማት የክፍያ ቅናሽ እያደረጉ ይገኛል። ከእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንዱ በሆነው በስካይ ላይት ሆቴል የህዝብ ግንኙነትና የማርኬቲንግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አማኑኤል አጋዥ በሆቴሉ የእንግዶች መኝታ ክፍል አገልግሎት ክፍያ ላይ ከ30 በመቶ ጀምሮ ቅናሽ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ታሪኩ ነጋሽ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት የቱሪዝም ፍሰቱ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን ከማጎልበት አንጻር የሚኖረውን ጠቀሜታ ገልጸዋል። በሚኒስቴሩ በ2011 ዓ.ም የአገር ውስጥ ቱሪዝም መመሪያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉን አንስተው በአዲሱ አመት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱንም አክለዋል።